ኢትዮ ቴሌኮም የ994 የጥሪ ማዕከል አገልግሎቱን ለውስን ደንበኞች ብቻ ክፍት እንዲሆን አደረገ 

በአማኑኤል ይልቃል

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹ ከጥሪ ማዕከል ሰራተኞች ጋር የሚገናኙበትን አገልግሎት፤ በከፊል የሚያስቀር አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ። በአዲሱ አሰራር መሰረት ከድርጅቱ የጥሪ ማዕከል ሰራተኞች ጋር የሚገናኙ ተገልጋዮች፤ “የፕሪሚየም እና የተለዩ አገልግሎቶችን የሚፈልጉ” ተብለው የተለዩ ደንበኞች ብቻ እንደሚሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

መንግስታዊው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አቅራቢ ድርጅት ከደንበኞቹ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ከሚሰጥባቸው አማራጮች ውስጥ አንዱ፤ ወደ ተቋሙ የጥሪ ማዕከል በ994 አጭር ቁጥር መወደል ነው። በዚህ ቁጥር ላይ የሚደውል ደንበኛ፤ በስልኩ ላይ በድምጽ የሚቀርብለትን  አማራጮች በመከተል የሚፈልገውን የአገልግሎት አይነት እንዲያገኝ ይደረጋል። ደንበኞቹ ከተቋሙ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችም፤ በመስመር ላይ የሚጠብቁ የጥሪ ማዕከሉ ሰራተኞች ምላሽ ይሰጣሉ። 

በቀን ለ16 ሰዓታት አገልግሎት የሚሰጠው የኢትዮ ቴሌኮም የጥሪ ማዕከል፤ በአንድ ቀን ውስጥ ከ350 እስከ 400 ሺህ ጥሪዎችን እንደሚያስተናግድ ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በመላው ሀገሪቱ ከ70 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም፤ ከአገልግሎቶቹ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች በተቋሙ ጥሪ ማዕከል ውስጥ ሆነው ምላሽ የሚያቀርቡ 1,300 ሰራተኞች አሉት። የማዕከሉ ሰራተኞች ከደንበኞች የሚመጡ ጥሪዎችን የሚያስተናግዱት በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሌኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ነው። 

የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ለጥሪ ማዕከሉ ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ “የፒን ቁጥርን ከመርሳት፣ የጥሪ ዝርዝርን ከመጠየቅ እንዲሁም ስልክ ቁጥር ከማስከፈት እና ከማዘጋት” ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የተቋሙ ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱላቸው የሚፈልጉ ደንበኞች መስመሩን ለረጅም ጊዜ ይዘው የሚቆዩ መሆናቸው እና ቁጥራቸውም በርካታ መሆኑ፤ ሌሎች “መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚጠይቁ ሰዎች” ከጥሪ ማዕከሉ ሰራተኞች ጋር እንዳይገናኙ ማድረጉን አስረድተዋል።

ይህን መሰል የደንበኞች ጥያቄ “በዲጂታል አማራጭ መመለስ የሚችሉ” መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ መሳይ፤ በዚህም ምክንያት ኢትዮ ቴሌኮም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ያስረዳሉ። “ይህ ነገር ለተገባው ሰው ብቻ መድረስ የሚገባው  ስለሆነ [ጥያቄ ለሚጠይቁት] በአማራጮች እያደረግን፤ የጥሪ ማዕከላችን ግን ይበልጥ ትኩረት በሰጠ መልኩ ለሌሎች ደንበኞቻችን የሚገኝ እንዲሆን እየተደረገ ነው” ሲሉም ተቋሙ እየተከተለ ያለውን አዲስ አሰራር አመልክተዋል።

በአዲሱ አሰራር መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች፤ 8994 የአጭር የመልዕክት ቁጥርን እና +251994000000 የዋትስአፕ ቁጥርን መመደቡን የተቋሙ ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አስረድተዋል። ከእነዚህ አማራጮች በተጨማሪም ጥያቄዎች የሚላኩበት የኢሜይል አድራሻ ተቋሙ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች በእነዚህ አማራጮች ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች፤ የተቋሙ ሰራተኞች በቀጥታ ምላሾችን እንደሚሰጡ አቶ መሳይ አክለዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም ጥያቄ ለሚያቀርቡ ደንበኞቹ፤ ከዚህ ቀደምም ምላሽ ሲያቀርብባቸው የቆየባቸውን የተቋሙን የማህበራዊ ትስስር ገጾች መጠቀሙን እንደሚቀጥል የድርጅቱ ቺፍ የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አስታውቀዋል። በተቋሙ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች “በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ” ምላሽ እንደሚሰጥ አቶ መሳይ አመልክተዋል። እነዚህ አማራጮች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሙሉ ሙሉ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፤ የጥሪ ማዕከሉም “ለፕሪሚየም ደንበኞች” እንዲሁም በአማራጮቹ ምላሽ ማግኘት ለማይችሉ ደንበኞች ብቻ ክፍት እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)