የልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተኪ ምርቶች የስራ አፈጻጸም በእቅድ ከተያዘው አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ  

ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶችን በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለማምረት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተይዞ የነበረው እቅድ የሶስት ወራት አፈጻጸም 53 በመቶ ብቻ መሆኑ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ። በዘንድሮ በጀት ዓመት ሶስት ወራት በልዩ ኢኮኖሚ ዞን በተመረቱ ተኪ ምርቶች ማዳን የተቻለው የገንዘብ መጠን 211 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ተብሏል። 

ይህ አሃዝ ይፋ የተደረገው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ህዳር 11፤ 2018 በተካሄደ ስብሰባ ላይ ነው። የፓርላማው የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው በዚህ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸሙን አቀርቧል።  

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት፤ በልዩ ኢኮኖሚ ዘርፍ ከሚመረቱ ተኪ ምርቶች በሩብ አመቱ ለማዳን ታቅዶ የነበረው 400 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ገልጸዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች 1.035 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶችን ማምረታቸውን አስታውቆ ነበር።

ኢንዱስትሪዎቹ ያዳኑት ገንዘብ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እጥፍ በላይ ነው። በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት፤ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጭ ከላኳቸው ምርቶች የተገኘው የገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ በእጥፍ የላቀ መሆኑ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተመልክቷል።

በሩብ ዓመቱ ከልዩ ኢኮኖሚ ዞን ኤክስፖርት ከተደረጉ ምርቶች የተገኘው የገንዘብ መጠን 49.8 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አቶ ዳጋቶ ገልጸዋል። ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሰጥታው የነበረውን ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ለመላክ የሚያስችል መብት (አጎዋ) ማቆሟን ለማካካስ በተወሰደ እርምጃ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን ከ“አጎዋ” ተጠቃሚነት በጥቅምት 2014 ዓ.ም. የሰረዘችው፤ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት “በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን ሰብዓዊ መብቶች በመተላለፍ ከፍተኛ ጥሰት ፈጽሟል” በሚል ነበር። ከ“አጎዋ” የንግድ ተጠቃሚነት መቆም በኋላ “የኤክስፖርት መቀዛቀዝ ታይቶ” እንደነበር አቶ ዳጋቶ በዛሬው ማብራሪያቸው ላይ አመልክተዋል።



ይህን ችግር ለመቅረፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ወጭ ሀገራት ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉ ድርጅቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ መደረጋቸውን አስረድተዋል። ድርጅቶቹ ኤክስፖርት ማድረግ በመቻላቸው በሪፖርቱ የተጠቀሰው ያህል ገንዘብ መገኘት መቻሉንም አክለዋል።

የፓርላማው የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተኪ ምርቶች ለማዳን የታቀደው የገንዘብ መጠን  ከአፈጻጸሙ ጋር ሲነጻጸር “ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት” ምን እንደሆነ ጥያቄ አቅርቧል። በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በኮሚሽኑ በኩል ምን እየተሰራ እየተሰራ እንደሆነም የተቋሙ አመራሮችን ጠይቋል።  

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር፤ “የእዚህ ዓመትን እቅድ ስናቅድ፤ ተኪ ምርት ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ ድርጅቶች የመለየት ስራ ሰርተን ነው ወደ ስራ የገባነው። ድርጅቶቹን ለይተናል። በየትኛው ዘርፍ ላይ መሳተፍ እንደሚገባ ዘርፎችን ከለየን በኋላ፤ ከድርጅቶች ጋር ቁጭ ብለን ውይይት አድርገናል። ይሄ በድርጅት የታቀደ ነው” ሲሉ እቅዱ ከድርጅቶች በተሰበሰበ አሃዝ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አብራርተዋል።  

“በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ይሄንን አለመፈጸም እንደማይቻል [ከድርጅቶቹ] ጋር ስለተግባባን፤ ቀሪ ወራት የቀሩ አፈጻጸሞችን ለማካካስ ከእነሱ ጋር እንሰራለን። የመጀመሪያው ሩብ አመት የተተኩትን [ምርቶች] ብቻ ቆጥረን compile ስላደረግን የመጣ ውጤት ነው” ያሉት አቶ ዳጋቶ፤ በመጪዎቹ ወራት በአፈጻጸም ላይ መሻሻል እንደሚኖር እና ተቋማቸው በእቅድ የያዘውን ያሳካል ብለው እንደሚያስቡ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)