የፌደራል ፖሊስ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት እንደማይሳተፉ “በተጨባጭ አረጋግጬያለሁ” አለ 

የፌደራል ፖሊስ ኮንትሮባንድን ለመከላከል ባደረጋቸው “ኦፕሬሽኖች”፤ በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግስት ኃላፊዎች ተሳትፎ እና “ኔትወርክ” የሌለበት መሆኑን “በተጨባጭ ማረጋገጡን” ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተናገሩ። የጸጥታ ተቋሙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን “የመያዝ አቅሙ” እንዳደገ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ባለፈው ዘጠኝ ወር ብቻ 20.5 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የወጪ እና የገቢ ንግድ ሸቀጦችን “በቁጥጥር ስር ማዋሉን” አስታውቀዋል። 

የፌደራል ፖሊስ ዋና አዛዡ ይህን ያስታወቁት፤ የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 21፤ 2018 ባቀረቡበት ወቅት ነው። ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ ህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድን የመከላከል “ሰፊውን ስራ የሚሰራው” የፌደራል ፖሊስ መሆኑን አመልክተዋል። 

ይህ ስራ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሚከናወን መሆኑንም ዋና አዛዡ ጠቁመዋል። በዚህ የቅንጅት ስራም በ2017 በጀት ዓመት 15.6 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የገቢ እና ወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን “በቁጥጥር ስር ማዋል” መቻሉን አስረድተዋል።    

ይህ አሃዝ በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወር ብቻ አምስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ጭማሪ ማሳየቱን ኮሚሽነር ጄነራሉ ለፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ31.3 በመቶ የላቀው ይህ የመከላከል ስራ፤ የፌደራል ፖሊስ በሚያከናውነው የ“ስምሪት እና ቁጥጥር” ስራ ላይ “ከፍተኛ እድገት” በማምጣቱ የተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።

ሪፖርቱ የቀረበለት የፓርላማው የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮንትሮባንድ የወንጀል ድርጊትን ለመከላከል የጸጥታ ተቋሙ ያከናወነው ስራ “የሚበረታታ” እንደሆነ ገልጿል። የኮንትሮባንድ ንግድን “አሳሳቢ” ሲል የጠራው ቋሚ ኮሚቴው፤ ችግሩን “ከመሰረቱ ለመፍታት እና ለመቀነስ” የተከናወኑ አብይት ተግባራትን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቋል። 

የፌደራል ፖሊስ ዋና አዛዥ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረጉ ኦፕሬሽኖች መገንዘብ የተቻለው “ትልቁ እና ዋናው ነገር”፤ በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ “በተለይም የመንግስት ኃላፊዎች ኔትወርክ የሌለበት መሆኑ” “በተጨባጭ፣ በኦፕሬሽን መረጋገጡ” እንደሆነ አስረድተዋል።

“ይህንን የምንልበት ምክንያት የመንግስት ኃላፊዎች በዚህ አይነት ተግባር ውስጥ የሚሳተፉ ከሆነ ኔትወርኩ ይሰፋል። የመያዝ አቅሙ ያንሳል። ኮንትሮባንድ እንደፈለገ የሚገባበት እድል ሰፊ ነው። ይሄ ከለውጡ በፊት ሁላችንም የምናውቀው፤ ኮንትሮባንድ እና እንደዚህ አይነት ስራዎች ውስጥ ‘ማን ነበር የሚሳተፈው?’ የሚለውን ነገር በግልጽ መረዳት ተገቢ ይሆናል” ሲሉ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ  የመንግስት አመራሮች ከዚህ ቀደም በህገወጥ ንግድ ሲሳተፉ እንደነበር በተዘዋዋሪ ፍንጭ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት “በግለሰብ ደረጃ በራሱ የሚሳተፍ ሆኖ የሚያዝ ካልሆነ በስተቀር”፤ በመንግስት ባለስልጣናት “ኔትወርክ” ደረጃ እንደ ቀደሙት ዓመታት ተሳትፎ እንደሌለም የፖሊስ ዋና አዛዡ አስገንዝበዋል። “በየትኛውም የሀገራችን ማዕዘን ላይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በስፋት ሲያዝ፤ በዚያ ውስጥ የተሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ [ነው]” ሲሉም ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ አክለዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው ጥር ወር ባወጣው መረጃ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ 729 በኮንትሮባንድ ተግባር ላይ በመሳተፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ 13 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዲሁም ህገ ወጥ ገንዘብ መያዙንም ሚኒስቴሩ በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር።

በኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በነበሩት ሰባት ዓመታት ብቻ 75 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ ንብረት መያዙን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የኮንትሮባንድ ንግድ “ሀገር እንዳይረጋጋ ከሚያደርጉ ቁልፍ ችግሮች” መካከል አንዱ መሆኑን የጠቆሙት የፓርላማው የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ፤ ይህን ተግዳሮት ለመቅረፍ የህግ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በፌደራል ፖሊስ “የተሰሩ ስራዎች” እና “የመጡ ውጤቶች” ጥሩ መሆናቸውን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፤ ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ ይብለጥ የተጠናከረ ስራ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። “አሁን በደረሳችሁበት የመጣ ውጤት ከትላንት ጋር የሚወዳደር አይደለም። ትላንትን አይደለም ማወዳደር ያለብን፤ በችግሩ ልክ ነው መነጋገር ያለብን። አሁንም የሚሾልኩ ነገሮች እንዳይኖሩ፤ ፖሊሲያዊ ጥበብን ተጠቅሞ በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል” ሲሉም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)