በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ትኩረት ከሳቡ አጀንዳዎች አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ፤ በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ልሂቃን እና በሌሎች ተመካካሪዎች መካከል አለመግባባት ፈጥሯል። “አዲስ አበባ የፌደራል ትሁን ወይስ የኦሮሚያ ክልል አካል?” የሚለው ጥያቄ በጉባኤው ከተደራጁ ጥቃቅን ቡድኖች እስከ ስልታዊ ቡድኖች ድረስ ተንጸባርቋል።
ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 22፤ 2018 ዓ.ም በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ በተካሄደው የፌደራል ከተሞች አጀንዳ ላይም ይኸው አከራካሪ ጉዳይ አነጋግሯል። በቁጥር 16 የሆኑት ስልታዊ ቡድኖች፤ እያንዳንዳቸው 250 ተመካካሪዎችን በውስጣቸው የያዙ ናቸው።
የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በተከታተለው የፌደራል ከተሞች አጀንዳ ምክክር ላይ የድሬዳዋ ከተማ ጉዳይ የተካተተ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ትኩረት የሳበው የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ መሆኑን አስተውሏል። በትላንቱ የምክክር ውሎ የአወያዮች ጣልቃ ገብነት የተመካካሪዎችን ሃሳብ ሲገድብ ታዝቧል።

አንደኛውን ስልታዊ ቡድን ይመራ የነበረው አወያይ፤ ተመካካሪዎች ከመወያያ ሰነዱ ውጪ የሆኑ የግል አስተያየቶችን ከመስጠት እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቅ ዘጋቢያችን ተመልክቷል። የትላንቱ ውይይት በርከት ያሉ ተመካካሪዎች “ሃሳባችን አልተካተተም” የሚሉ ድምጾችን ያሰሙበትም ነበር።
ከእነዚህ ተመካካሪዎች አንዱ የሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ የተወከሉ የጉባኤው ተሳታፊ “በንዑስ ቡድን ተወያይተን ነገር ግን የተደራጀው አጀንዳ ምክረ ሐሳብ ላይ አልተካተተም” በማለት ቅሬታ አቅርበዋል። “በንዑስ ቡድናችን አዲስ አበባ የፌደራል ዋና ከተማም፣ የኦሮሚያ [ክልል] ዋና መቀመጫ ሆና እንድትቀጥል የሚል ሐሳብ ሰጥተን ነበር። ነገር ግን ከመድረክ ይህ ጉዳይ ባለመነሳቱ ሊካተት ይገባል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው የመጡ ሌላ ተመካካሪ ሃሳባቸውን በኦሮምኛ ቋንቋ ካቀረቡ በኋላ በአስተርጓሚ አማካኝነት አስተያየታቸው ተደምጧል። የቀረበው ሰነድ “አካታች አይደለም” ያሉት እኚሁ ተመካካሪ፤ “አጀንዳዎቼ በሚገባ አልቀረቡም፣ ተንጠባጥበዋል” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

“በውይይታችን ውስጥ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ናት ብለን ወስነን ነበር። ይህ ከተደራጀው ሰነድ ላይ በትክክል ግልጽ ተደርጎ አልተንጸባረቀም። ሌላው አዲስ አበባ የኦሮሚያ እምብርት ናት የሚለውን በግልጽ ለመግለጽ መሸርኮመም ተመልክቻለሁ። ይህ ሊስተካከል ይገባል” ሲሉ በአስተርጓሚ በኩል ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
ይህን ተከትሎ የመድረኩ አወያዮች፤ ከግል አስተያየት በመውጣት በቀረበው ሰነድ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲደረግ አሳስበዋል። አስተርጓሚው በጉባኤው ተሳታፊ የተነሳውን አስተያየት በመቀጠል “ ‘አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ስር ከገባች ለብሔር ብሔረሰቦች ስጋት ትሆናለች’ በሚል የቀረበው ሃሳብ መስተካከል አለበት። ብሔር ብሔረሰቦች በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም ያሉት። በኦሮሚያ ሁሉም ከተሞች ይገኛሉ። ለምን የአዲስ አበባ ሲሆን ይህ ይነሳል?” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ተወካዩ ያቀረቡትን ጥያቄ አስተጋብተዋል።
ይኸው “የስጋት ጉዳይ” በሌላ ስልታዊ ቡድን በታቀፉ ተመካካሪ ዘንድም ቅሬታ አስነስቷል። ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን የወከሉት ተመካካሪው “ ‘አዲስ አበባ ኦሮሚያ ስር ብትሆን ለሌሎች ህዝቦች ስጋት ይፈጥራል’ የሚለው የተሳሳተ ነው። ኦሮሞ ለሌሎች ሕዝቦች ስጋት አይደለም። እንኳን የኦሮሚያ ህዝብ የኬንያ ህዝብ ሥጋት አይደለም። ምናልባት ግብጽ ስጋት ብትሆን ነው። ይህ ቃል እንዲደገም አንፈልግም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እኚሁ ተመካካሪ በየቀረበው የአጀንዳ ምክረ ሃሳብ ላይ ቅሬታ እንዳላቸውም ገልጸዋል። አጀንዳ እንዲያደራጁ የተመረጡት 25 ተመካካሪዎች ማንነት “ስብጥር የሌለው ይመስለኛል” ያሉት የጉባኤው ተሳታፊ፤ ለዚህም እርሳቸው በንዑስ ቡድናቸው የተወያዩባቸው ጉዳዮች አለመቅረባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
“የአዲስ አበባ ጉዳይ ከፌደራል ስርዓቱ አንጻር መታየት አለበት” የሚል ሐሳብም ማቅረባቸውን የጠቀሱት እኚሁ የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ይህ ሃሳባቸው በሰነዱ ላይ አለመካተቱን አስረድተዋል። “አዲስ አበባ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ላይ የመንግሥት ርዕሰ ከተማ ናት የሚል ነው። በዚህ አጀንዳ ዙሪያ የተደረገው ውይይት በቀረበው [ምክረ] ሐሳብ ላይ አልሰማሁም” ብለዋል።
“የአንድ ክልል መሬትን ለፌደራል አንስቶ መስጠት፤ ነገ ሌሎች ክልል ከተሞች ለፌደራል ይስጡ ሊባል ነው? ይህ መታየት አለበት” ሲሉም ተመካካሪው አሳስበዋል። በምክረ ሃሳቡ ላይ የተዛባ አቀራረብ በመኖሩ ሪፖርቱ እንደገና እንዲስተካከልም ጠይቀዋል።

ተመካካሪው የጠቀሱት የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 49 በውስጥ የያዛቸው ድንጋጌዎች፤ የፌደራል ርዕሰ ከተማን የተመለከቱ ናቸው። በዚሁ አንቀጽ የፌደራል መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ መሆኗን ተደንግጓል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት ቢሆንም አስተዳደሩ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን እንዳለው በዚሁ አንቀጽ ላይ ተቀምጧል።
በ1987 ዓ.ም የጸደቀው ህገ መንግስት፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በፌደራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚወከሉም ይገልጻል። በምክክር ጉባኤው እያከራከረ ያለው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ጉዳይ ላይም፤ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ላይ በጥቅሉ ተነስቷል።
“የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” ሲል ህገ መንግስቱ ደንግጓል።
“የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል”
የኦሮሚያ በአዲስ አበባ ክልል ያለውን “ልዩ ጥቅም” የተመለከተ ህግ የማውጣት ሙከራዎች ከዚህ ቀደም መደረጋቸው ቢገለጽም፤ በህገ መንግስቱ ቃል በተገባው መሰረት እስካሁን ድረስ በይፋ የወጣ አዋጅ የለም። በትላንትናው የምክክር ውሎ ከአዲስ አበባ ከተማ የተወከሉ ተሳታፊ “በልዩ ጥቅም” ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት አቅርበዋል።
“ ‘ልዩ ጥቅም’ የሚለው አያስማማም፤ እንደ አማራጭ ‘ተገቢው የካሳ እና የአገልግሎት ክፍያ’ በሚል እንዲቀመጥ ተብሎ የተወያየንበት አልተካተተም” ሲሉ እኚሁ ተሳታፊ ተናግረዋል። “የኦሮሚያ ህብረተሰብ ጥያቄ እንዲሁ ልዩ ጥቅም ይሰጠኝ ሳይሆን፤ ተገቢው ካሳ እና ተገቢው የአገልግሎት ክፍያ ይሰጠኝ ነው። በመሬቴ ላይ ፋብሪካ ሲቆም፣ ኢንቨስት ሲደረግበት እዚያ ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት በቅርበት ላግኝ የሚል ጥያቄ ነው” ሲሉም የአዲስ አበባው ተወካይ ገልጸዋል።
እኚሁ ተመካካሪ “አዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ሳይሆን ልዩ ድጎማ ያስፈልጋታል” ሲሉም ተደምጠዋል። “አዲስ አበባ ከፌደራል እና ከሁሉም ክልሎች ድጎማ ያስፈልጋታል። አዲስ አበባ ‘የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ከተማ’ ከተባለች፤ ክልሎች አዲስ አበባ ላይ ዕዳ አለባቸው። የልጅ ልጆቻቸውን ይዛ እያኖረች በመሆኑ ክልሎች መደጎም አለባቸው የሚለው ሃሳብ ይያዝልኝ” ብለዋል።

“አዲስ አበባ የሁሉም ናት” ያሉት ተመካካሪው፤ “የአንድ አካል ካደረግናት ትጠፋለች” ሲሉ መረር ያለ ሃሳብ ሰንዝረዋል። ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ተወካይ በበኩላቸው “በጥርጣሬ እና በስጋት” በሚል ከቤቱ የቀረቡ አስተያየቶች በድጋሚ መታየት እንዳለባቸው አስገንዘበዋል። እንደዚህ አይነት አስተያየቶች “አቀራራቢ አይደሉም” ሲሉም እንደሌሎች ተሳታፊዎች ሁሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
“ለ15 ዓመታት በኖርኩባት አዲስ አበባ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ፖሊስ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ፍርድ ቤት እና የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ሲጋጩ ተመልክቼ አላውቅም። በመሆኑም የሚቀርቡ ሃሳቦች ጥንቃቄ ይደረግባቸው” ሲሉም ተመካካሪው አሳስበዋል።
የሲዳማ ክልል የመንግሥት ተቋምን ወክለው በሀገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ደምሴ ደንጊሶ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ትሁን ወይስ የፌደራል?” የሚለው ሃሳብ እርሳቸው በነበሩበት ቡድን ከፍተኛ ክርክር ያስነሳ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሌላ በኩል አዲስ አበባ “በኦሮሚያ ክልል እምብርት ላይ ያለች በመሆኗ”፤ በህገ መንግስቱ የተቀመጠው የልዩ ተጠቃሚነት ድንጋጌ አንቀጽ “ተግባራዊ መሆን አለበት” የሚል ብርቱ ክርክር መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ደምሴ እርሳቸው በተሳተፉበት ቡድን በብዛት የተንጸባረቀው ሃሳብ “አዲስ አበባ የፌደራል ከተማ ትሁን” የሚለውን የሚደግፍ እንደሆነም አክለዋል። “[አዲስ አበባ] ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ የያዘች ከተማ ብሎም የአፍሪካ ዋና ከተማ በመሆኗ፤ ይህ የአዲስ አበባ ሀብት ሁሉም ያፈራው በመሆኑ፣ ወደ ታች ወስዶ ማቀጨጭ አስፈላጊ አይደለም” ሲሉም አቋማቸውን አጋርተዋል።
የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ወሕዴፓ) ወክለው በፌደራል ከተሞች ጉዳይ ላይ እየተወያዩ የሚገኙት ኮሎኔል አለማየሁ ኃይሌ፤ የህገ መንግስቱ “የልዩ ጥቅም” ድንጋጌ ተግባራዊነት ላይ በእርሳቸው ቡድን ደረጃ ላይ ከስምምነት ላይ መደረሱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም በሌሎች ቡድኖች ይህ ሃሳብ ተቃውሞ እንደገጠመው እና “አዲስ አበባ ራስ ገዝ ሆና እንድትቀጥል” የሚሉ ሃሳቦች እንደተነሱ መስማታቸውን ጠቅሰዋል።
“በህገ መንግስቱ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የሚያገኘው ‘ልዩ ጥቅም’ የሚለው ጉዳይ ስሙ ብቻ ነው የተቀመጠው። ስለዚህ ካልተተገበረ አለማስቀመጥም ይቻል ነበር። በመሆኑም አሁንም አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ እንደመገኘቷ ልዩ ተጠቃሚነቷ መረጋገጥ አለበት የሚል ጽኑ አቋም አንጸባርቀናል” ያሉት ኮሎኔል አለማየሁ፤ በቀጣይ ያሉት ጉዳዮች በሌሎች ውይይቶች መፍትሔ ያገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።
በትላንትናው የምክክር ውሎ የአዲስ አበባ ስያሜ እንዲለወጥ፣ የከተማይቱ የአካባቢ ስሞች እንዲቀየሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት እና የከተማይቱ ፖሊስ በድጋሚ እንዲዋቀሩ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል። በምክክር ጉባኤው ላይ “ግላዊ ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል” የሚል ትችት የቀረበ ሲሆን ከውይይት ሰነዱ ውጪ ያሉ ሃሳቦች ጥንቃቄ እንዲደረግባቸውም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























