ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ መመዝገቡን ይፋ አደረገ

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (ESX) ላይ የተመዘገበ አራተኛው ኩባንያ ሆነ። ተቋሙ በዚህ ገበያ ላይ መመዝገቡን ይፋ ያደረገው ከኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ጋር በመተባበር ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 18፤ 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባው ስካይላይት ሆቴል በሰጠው የጋራ መግለጫ ነው።

እስካሁን በሀገሪቱ የመጀመሪያውና ብቸኛው የተደራጀ የካፒታል ማርኬት የሆነው እና በመንግሥትና በግል አጋርነት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ በይፋ ተመዝግበው ተሳታፊ የሆኑት ሦስት የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ነበሩ። የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ በይፋ ሥራ መጀመሩ በተበሰረበት በጥር 2017 ዓ.ም.፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያው ላይ መመዝገቡ የተገለጸው ወጋገን ባንክ ነበር።

ከወጋገን ባንክ ምዝገባ ስድስት ወራት በኋላ ገዳ ባንክ፣ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ አዋሽ ባንክ በዚሁ ገበያ ላይ መመዝገባቸው ይፋ ተደርጓል። ኢትዮ ቴሌኮም አራተኛ ተቋም ሆኖ በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ ከመመዝገቡ አስቀድሞ 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖቹን ለሽያጭ ገበያ አውጥቶ ነበር።

ኩባንያው ባለፈው ሚያዝያ ወር ባወጣው መግለጫ ለአራት ወራት ያህል ክፍት ሆኖ በቆየው በዚህ የሽያጭ ሂደት ለሽያጭ ካቀረበው የ10 በመቶ የኩባንያው ድርሻ ውስጥ 10.7 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ብቻ የተሸጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 89.3 ሚሊዮን አክሲዮኖች ግን ሳይሸጡ ቀርተዋል። በተመሳሳይ ተቋሙ ከአክሲዮን ሽያጩ 30 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የቻለው ግን 3.2 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ መግለጹ አይዘነጋም።

በዚህ የሽያጭ ሂደት ላይ ከ47 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን መግዛታቸውን ተቋሙ በወቅቱ አስታውቋል። አክሲዮን ከገዙ ዜጎች ውስጥ 45,336 የሚሆኑት “የባለቤትነት ማረጋገጫ” እና “አክሲዮኖችን ወደ ዲጂታል የመቀየር (dematerialization)” ሂደታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸው በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል።

የባለቤትነት ማረጋገጫ ሂደታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች አክሲዮኖች በገንዘብ ሲሰላ 3.04 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መሆናቸውንም ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል። አክሲዮን ከገዙ ባለሀብቶች ውስጥ 3.4 በመቶ የሚሆኑት የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ባለማቅረባቸው እና ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው በመሆኑ፤ ለአክሲዮን ግዢ የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ እንደሚደረግላቸው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ላይ መመዝገቡን ተከትሎ፤ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን በገበያው ላይ ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ዝግጅት መጠናቀቁን ተቋሙ ዛሬ ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸውን የመሸጥ፣ የመግዛት እንዲሁም የማስተላለፍ (transfer) መብት የሚያገኙ ይሆናል። 

በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ አክሲዮኖቻቸውን ለመሸጥም ሆነ ተጨማሪ ለመግዛት የሚፈልጉ ባለአክሲዮኖች፤ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ፈቃድ ከተሰጣቸው “አገበያዮች” ወይም “የኢንቨስትመንት ባንኮች” ዘንድ በመቅረብ “የንግድ አካውንት” በመጀመሪያ መክፈት ይገባቸዋል። የባለቤትነት ድርሻቸውን “ወደ ዲጂታል የመቀየር” ሂደትን ያጠናቀቁ ባለአክሲዮኖች፤ የባለቤትነት መብታቸው ከዘንድሮው በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ “የሚከበር” እና “የሚጠበቅላቸው” መሆኑንም ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል። 

ኩባንያው የ2018 በጀት ዓመት “አፈጻጸሙን” እና “የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርቱን” ለባለአክሲዮኖች እና ለደንበኞቹ እንደሚያሳውቅም ገልጿል።  የመጀመሪያውን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በመጪው በጀት ዓመት እንደሚያካሄድ የጠቆመው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዚሁ ስብስባ ላይ “የትርፍ ክፍፍል” እና “ሌሎች ስትራቴጂያዊ ውሳኔዎች” ለባለድርሻዎች ይፋ እንደሚደረጉ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]