ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ እንዲቆይ” ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በአጀንዳነት ማቅረቡን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አረጋገጡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣዩ የመንግስት ምስረታ ወቅት የበዓለ ሲመት ክብረ በዓል እንደማይኖርም ገልጸዋል።
አብይ ይህን ያሉት፤ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 30፤ 2018 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው። በዚሁ የፓርላማ ስብሰባ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ ምርጫን በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔ እና በሀገራዊ ምክክር ላይ ያቀረበው አጀንዳ ይገኝበታል።
ከአንድ ሳምንት በኋላ መካሄድ በሚጀምረው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ ብልጽግና ፓርቲ ለውይይት ካቀረባቸው አጀንዳዎች መካከል የስልጣን ገደብ አንዱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ፓርቲው “በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ቢበዛ ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ መቆየት አለበት” የሚል አጀንዳ ማቅረቡን የገለጹት አብይ፤ ይህ በአፍሪካ አህጉር ያልተለመደ እንደሆነ አመልክተዋል።
“በአፍሪካ ደረጃ ህገ መንግስት አሻሽለው እድሜ ሲያራዝሙ እንጂ፤ ያልተገደበ እድሜ ኖሯዋቸው እድሜ ሲገድቡ ሰምተን አናውቅም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። አሁን በስራ ላይ ባለው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ገደብ በግልጽ አልተቀመጠም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ፤ ፓርቲያቸው ያቀረበውን አጀንዳ “ታላቅ እርምጃ”፣ “ለሀገር የሚጣል ጡብ” እና “መሰረት ነው” ሲሉ አሞካሽተዋል። “አሁን ባለው ስሜት በተሟላ መንገድ መገንዘብ ብንቸገርም፤ ውለን ስናድር ለልጆቻችን አስተማማኝ መሰረት ስለሆነ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል” ሲሉም አብዛኞቹ የብልጽግና ፓርቲ ተመራጭ ለሆኑት ተሰናባቾቹ የፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
አብይ የመንግስት የስልጣን ገደብን በተመለከተ ሲናገሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ከእርሳቸው እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ አንስተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ስብሰባ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የአስፈጻሚው አካል ያለው የስልጣን ዘመን በህግ ሊገደብ እንደሚገባ እና ይህ ጉዳይ በምክክር ሂደቱ ውስጥ ሊካተት የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተው ነበር። “በህገ መንግስቱ ማሻሻያ መሰረት የእዚህ ሀገር መንግስት የስልጣን ጊዜ እንዲገደብ ግንባር ቀደም ፈላጊዎች ነን። መገደብ አለበት ብለን እናምናለን። በዚህ ህግ መሰረትም እንዲፈጸም እንሰራለን” ሲሉ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል።
አብይ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ያነሱት ሌላ ጉዳይ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር የሚደረገውን በዓለ ሲመት ክብረ በዓል የተመለከተ ነው። ባለፈው ወር የተካሄደውን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ፤ በመጪው መስከረም ወር የመንግስት ምስረታ ሲያካሄድ የበዓለ ሲመት ዝግጅት እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያቸው ይፋ አድርገዋል።
“ታስታውሱ ከሆነ ባለፈው አምስት ዓመት ምርጫ አሸንፈን፣ አጠቃላይ ዓለም ላይ ባለው ፖለቲካል አውድ፣ ‘በዓለ ሲመት’ ብለን እንግዶች ጋብዘን፣ አክብረን ነበር። በሚቀጥለው ጊዜ ግን እንደዚያ አይነት ጊዜ ማባከን አስፈላጊ ነው ብዬ እኔ አላምንም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። “ፓርላማ ጠዋት የሚመርጠውን ከመረጠ በኋላ ወዲያው ወደስራ መግባት እንጂ እንግዳ ስንቀበል፣ እንግዳ ስንሸኝ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ አይደለም” ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጠት ሂደት ከተከናወነባቸው 501 ወንበሮች መካከል ገዢው ብልጽግና ፓርቲ 438 መቀመጫዎችን ጠቅልሎ ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሁለት ሳምንት በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም። በዚሁ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 40፣ የግል ተወዳዳሪዎች ደግሞ 8 ወንበሮች ማግኘታቸውን ቦርዱ በወቅቱ ገልጿል።
በግንቦት ወር መጨረሻ በተደረገው ምርጫ ህዝብ ባለፈው “ስራ ስሩልን” ብሎ ድምጽ መስጠቱን ያስታወሱት አብይ፤ ከምርጫ በኋላ በቀጥታ ወደ ስራ መግባት የተሻለ አካሄድ መሆኑን አስገንዝበዋል። “መዘጋጀት የሚገባው ለምርጫው ነው። ካሸነፍን በኋላ ዘሎ ወደ ስራ እንጂ ለድግሱ የሚጠፋው ጊዜ ቢቀር ነው የሚሻለው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ክብረ በዓሉ “በሌሎች ሀገራት” ጭምር “ቢቀር” ጥሩ እንደሆነ ምክራቸውን ለግሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































