በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት እንዲቀሰቀስ “ሰፊ ፍላጎት” እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በደርግ ዘመነ መንግስት “ሻዕቢያ እና ወያኔ፣ ከሱዳን ጋር ተባብረው” የወቅቱን አገዛዝ መጣላቸውን እና አሁንም ተመሳሳይ “ምኞት” እንዳለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ “ሌላም ቢጨመር በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት ተሰናባቾቹ የፓርላማ አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ነው። ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 30፤ 2018 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻ መደበኛ ስብሰባ ላይ 18 የፓርላማ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በዛሬው ስብሰባ ያነሱት ገነት ቤተ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን፣ “አክራሪ” ሲሉ የጠሩትን የህወሓት ቡድን ሰሞነኛ ድርጊቶችን፣ ያታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴን እና የግጭት ቅስቀሳዎችን ጠቅሰዋል። በክልሉ “ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ” መንግስት በአሁኑ ወቅት እየወሰዳቸው ያሉ “ተጨባጭ እርምጃዎች እና የወደፊት እቅዶች” ምን እንደሆነ ጠይቀዋል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በማብራሪያቸው በቅድሚያ ያነሱት በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በጥቅምት 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመውን የግጭት ማቆም ስምምነት ነው። ስምምነቱ “እንደ ድርድር ብቻ መታየት ያለበት ጉዳይ ብቻ አይመስለኝም” ያሉት አብይ፤ “ብዙ ውጤት ያስገኘ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውጤቶች መካከል በትግራይ ክልል የተቋቋመው “ጊዜያዊ አስተዳደር” አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል። በትግራይ ክልል “አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር” እንዲመሰረት የሚያስችል ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው በመጋቢት 2015 ዓ.ም ነበር።
ደንቡ መጽደቁን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንዲመሩ ተሾመዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለሁለት ዓመት በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ጌታቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተከናወነ ስልጣናቸውን ምክትላቸው ለነበሩት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በመጋቢት 2017 ዓ.ም አስረክበዋል።
አንድ ዓመት በፕሬዝንዳትነት የቆዩት ሌተናል ጄነራል ታደሰ፤ የስልጣን ዘመናቸው ለተጨማሪ አንድ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቢራዘምላቸውም በክልል መሪነታቸው መቆየት አልቻሉም። በምትኩ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፤ ላለፉት ሁለት ወራት ክልሉን እየመሩ ይገኛሉ።
ዶ/ር ደብረጽዮን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትነት ስልጣንን የተቆጣጠሩት፤ ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት በሚያዝያ ወር መጨረሻ ክልሉን እንዲመሩ ከሾማቸው በኋላ ነበር። ከዚህ ሹመት በኋላ የፌደራል መንግስትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይፋዊ አቋማቸውን እስካሁን በግልጽ ሳያሳውቁ ቆይተዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ህወሓትን በስም ጠርተው ጠንከር ያሉ ትችቶችን ሰንዝረዋል። ህወሓት የ50 አመት አንጋፋ ፓርቲ መሆኑን ያስታወሱት አብይ፤ ፓርቲው “ወጣቱን ትውልድ ማመን ካልቻለ ኪሳራ ነው” ብለዋል።

“ይሄ የሚያኮራ ነገር አይደለም፤ የሚያሳፍር ነገር ነው። 50 አመት ፓርቲ መርተህ፣ ፓርቲ የሚተኩ ሰዎች ካልፈጠርክ ሌላ 1000 ቢሰጥህ አትፈጥርም ማለት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህ የሚያሳየው ነገር፤ አዲስ አስተሳሰብን፣ አዲስ ደምን እና አዲስ አቅጣጫን የማይቀበል ኃይል፤ በነበረው ነገር የትም አይደርስም” ሲሉ የህወሓት ወቅታዊ ቁመና አጣጥለዋል።
በትግራይ ክልል ባሉ ኃይሎች አማካኝነት በየቀኑ በርካታ ጦርነትን “ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች እየተፈጸሙ” መሆኑን በዛሬው ንግግራቸው የጠቀሱት አብይ፤ ማብራሪያቸውን ሲያደምጡ ለነበሩት የፓርላማ አባላት ከህወሓት ማሸነፍን “በፍጹም አትጠብቁ” ብለዋቸዋል። “ድል እና TPLF አራምባ እና ቆቦ ናቸው” ሲሉም አክለዋል።
“በትግራይ ጦርነት እንዲፈጠር ሰፊ ፍላጎት አለ” ያሉት አብይ፤ “ትላንትና ሻዕቢያ እና ወያኔ ከሱዳን ጋር ተባብረው ደርግን ጥለዋል። አሁንም እንደዚያ ተባብረን እንጥላለን የሚል ምኞት አለ” ሲሉ ተደምጠዋል። “እንኳን ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ሱዳን ሌላም ቢጨመር በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለም” ሲሉም በፓርላማ አባላት በጭብጨባ የታጀበ ንግግር አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን “ለመከላከል የሚያስችል ብቃት እየገነባን ነው ያለነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ አቅም “ጊዜው ሲደርስ እንደ አስፈላጊነቱ” እንደሚገለጽ ተናግረዋል። “እኛ ስጋት የለብንም” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ በድጋሚ ማስተማመኛ የሰጡት አብይ፤ “ጦርነት እምቢ ያልንበት ምክንያት ትርፍ የለውም ብለን ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው፤ በትግራይ ያለውን ችግር በውይይት እና በንግግር ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። “አሁንም ለሰላም በራችን ክፍት ነው። ለንግግር በራችን ክፍት ነው። መወያየት ነው የምንፈልገው። ሰላም ማምጣት ነው የምንፈልገው። በእኛ በኩል ትተን፣ ተጎድተን፤ ለትግራይ ሰላም ከመጣ ፍላጎታችን እሱ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































