ኢዜማ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ምክረ ሃሳቦችን የሚከታተል “ገለልተኛ እና ህጋዊ” አካል አንዲቋቋም ጠየቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን አተገባበር የሚከታተል “ገለልተኛ እና ሕጋዊ” አካል አንዲቋቋም ጥያቄ አቀረበ። የፌደራል መንግስት ምክረ ሃሳቦቹን ለመተግበር “ከተገቢው በላይ ጊዜ እንዳይወስድ” እና አፈጻጸሙን “በፍጥነት” እንዲከናወን እንዲያደርግም ፓርቲው አሳስቧል። 

ኢዜማ ማሳሰቢያውን እና ጥያቄውን ያቀረበው፤ ለ38 ቀናት ሲካሄድ የቆየውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጠናቀቀውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 20፤ 2018 በሰጠው መግለጫ ነው። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው ሀገራዊ የምክክር ሀሳቡ “ከተጠነሰሰበት ቀን” ጀምሮ “በከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት፣ በንቃት እና በሙሉ ቁርጠኝነት ሲሳተፍ መቆየቱን” አስታውቋል።

አራት ሺህ ሰዎች በተሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይም፤ ፓርቲው በመሪው አቶ እዮብ መሳፍንት፣ በሌሎች አመራሮቹ እና አባላቱ ተወክሏል። የጉባኤ ሂደቱን “ረጅም” እና “እልህ አስጨራሽ” ሲል በዛሬው መግለጫው የጠራው ኢዜማ፤ በምክክሩ ወቅት “በርካታ ስልታዊ ማነቆዎች” እና “አሰራርን ያላከበሩ ችግሮች” እንዳጋጠሙት አመልክቷል።

ፓርቲው ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው በጉባኤው “በኤክስፐርትነት” እና “በአስተባባሪነት” በተመደቡ የተወሰኑ ግለሰቦች ተፈጽሟል ያለውን የአሰራር ችግር ነው። ግለሰቦቹ በምክክሩ ሂደት ወቅት “ግልጽ ወገንተኛነት” እና “የተዛባ አካሄድ” ያንጸባርቁ ነበር ሲል ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ወንጅሏል።

በምክክሩ ሂደት እንዲህ አይነት ችግሮች መስተዋላቸውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሲገልጹ ቆይተዋል። እንደ ኢዜማ ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ ውስጥ ተወካይ ያለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጉባኤው በተጠናቀቀበት ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በምክክር ሂደቱ “ጥሰቶች” እና “አድሏዊ ጣልቃ ገብነቶች” መታየታቸውን በመግለጽ ድርጊቶቹን “አጥብቆ ተቃውሟል።

በዚያኑ ዕለት መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲም፤ ሀገራዊ የምምክር ጉባኤው “በመርህ እና በስክነት” የተካሄደ ሳይሆን “የእነ አጼ በጉልበቱ ትዕይንት ነው” ሲል ኮንኗል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንንም “ራሱ ላስቀመጠው መርህ እንኳን የማይገዛ” ፓርቲው ወቅሷል።

እናት ፓርቲ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ “መስመሩን የሳተ እንደሆነ” በመግለጽ፤ “የተዛነፈው አካሄድ መስመር እንዲይዝ” አቅጣጫዎች ሲጠቁም መቆየቱን በመግለጫው አስታውሷል። ሆኖም ፓርቲው እና ሌሎች መሰል ተቋማት ያቀረቧቸው “ምክንያታዊ የእርምት አስተያየቶችን” በበጎ ከመቀበል ይልቅ “ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሏል” ሲል በመግለጫው ጠቅሶ ነበር።

ኢዜማ በበኩሉ በምክክር ሂደቱ ያጋጠሙትን ችግሮች “ወደ አደባባይ ከማውጣት” ይልቅ፤ ቅሬታዎቹን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምክር ቤት የማቅረብ አካሄድ ሲከተል እንደቆየ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። ከኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአካል በመገናኘት “የማረሚያ ሀሳቦች” ማቅረቡንም ፓርቲው ጨምሮ ገልጿል።

በዚህ መንገድ “በርካታ ችግሮችን” መፍታቱን የገለጸው ኢዜማ፤ ሂደቱን እስከ ፍጻሜው ለማድረስ “ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለናል” ብሏል። በጉባኤው ሂደት በስምንት የምክክር ቡድኖች በውይይት የጎለበቱ ምክረ ሃሳቦች፤ አራት ሺህ ተመካካሪዎች ላሉበት ጠቅላላ ጉባኤ በማጠናቀቂያው ዕለት መቅረባቸውን ፓርቲው በመግለጫው አስታውሷል።

ለጠቅላላ ጉባኤ ከቀረቡ ምክረ ሃሳቦች የሚቀበለው ግን የምክክር ቡድኖች “በሙሉ ድጋፍ የፈረሙበትን” ብቻ እንደሆነ ኢዜማ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። ፓርቲው ይህን ያለበትን ምክንያት በመግለጫው ባይጠቅስም፤ በጉባኤ ላይ የተሳተፉ ተመካካሪዎች ግን ውዝግብ እና አለመግባባት ፈጥሮ የቆየው የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የምክክር ቡድኖች ካቀረቡት ውጪ ሌላ ምክረ ሃሳብ እንዲካተት መደረጉን ተናግረዋል። 

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው በጉባኤው ላይ በተመካካሪዎች የቀረቡ 400 ምክረ ሀሳቦችን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ” ጠይቋል። 2014 ዓ.ም የወጣው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ኮሚሽኑ “የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን” ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ደንግጓል።  

ኮሚሽኑ “የመጨረሻ ምክረ ሃሳቦችን” ለመንግስት እና ለህዝብ በሚያቀርብበት ወቅት፤ በአጠቃላይ የምክክሩን መንፈስ እና በንባብ የቀረበውን የተመካካሪዎችን “የመጨረሻ ምክረ ሃሳብ ብቻ ባከበረ መልኩ” እንዲሆን ኢዜማ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል። “የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ውጤታማ የሚሆነው የቀረቡት ምክረ ሀሳቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረጉ መሆኑን” በመግለጫው አጽንኦት የሰጠው ኢዜማ፤ የፌደራል መንግስት ምክረ ሃሳቦቹን ለመተግበር “ከተገቢው በላይ ጊዜ እንዳይወስድ” ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

መንግስት የምክረ ሃሳቦቹን አፈጻጸም “በፍጥነት” እንዲያከናወን እንዲያደርግም ፓርቲው በተጨማሪነት ጠይቋል። ኢዜማ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና ለፌደራል መንግስት ያቀረባቸውን ባለ አምስት ነጥብ ማሳሳቢያዎች ያጠቃለለው፤ በምክክር ጉባኤ ላይ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን አተገባበር የሚከታተል “ገለልተኛ እና ህጋዊ” አካል አንዲቋቋም ጥያቄ በማቅረብ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]