በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ አቀራራቢ ሃሳቦችን እንዲያዘጋጅ የተቋቋመው ኮሚቴ፤ አስማሚ ምክረ ሃሳቦችን ዛሬ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ውዝግብ እና አለመግባባት በፈጠረው የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ላይ አስማሚ ሃሳብ እንዲያዘጋጅ የተቋቋመው አቀራራቢ ኮሚቴ፤ የደረሰበትን ውጤት በዛሬው ዕለት ለተመካካሪዎች እንዲያቀርብ መወሰኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ኮሚቴው አስማሚ ሃሳቡን የሚያዘጋጀው፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ደረጃዎች የተከፋፈሉ ቡድኖች ያቀረቧቸውን ሃሳቦች ከቃለ ጉባኤዎች ላይ ከመረመረ በኋላ ነው ተብሏል።

በስምንት ዋነኛ አጀንዳዎች ተከፍሎ ላለፉት 35 ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ የአዲስ አበባ ከተማን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው በፌደራል ከተሞች ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲመካከሩ በተመደቡ ቡድኖች አማካኝነት ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ላይ ከ10 ጀምሮ እስከ 500 ተመካካሪዎችን የያዙ በድኖች ባካሄዷቸው ምክክሮች ያቀረቧቸው ምክረ ሃሳቦች፤ በተጠቃለለ የጉባኤው አንድ ወጥ ሰነድ ላይ ተካትቶ በትላንትናው ዕለት ለ4 ሺህ ተሳታፊዎች ይቀርባል ተብሎ ነበር። 

ሆኖም የኦሮሚያ ክልል ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ አጀንዳ ላይ ባቀረቡት አቤቱታ ሳቢያ፤ ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች በተገኙበት ሊደረግ የነበረው ስብሰባ ሳይካሄድ ቀርቷል። ከኦሮሚያ ተወክለው የመጡ ከ500 የሚልቁ ተመካካሪዎች የተቃውሞ ፊርማ የተካተተበት አቤቱታ፤ “አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ትሁን የሚለው በህገመንግስቱ ዕውቅና ይሰጠው” የሚል ይዘት ያለው እንደሆነ ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

 የአቤቱታው መቅረብ እስካሁን ስብሰባ ሳያደርግ የቆየውን “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” ወደ መድረኩ ያመጣ ሆኗል።  የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጀው ባለ ሁለት ደረጃ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅር አካል የሆነው “የክልል ተወካዮች ጉባኤ”፤ በሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ቀርበው “ስምምነት ያልተደረሰባቸው” አጀንዳዎች ላይ “የመጨረሻ ውሳኔ” ወይም “ምክረ ሃሳብ” የማሳለፍ ኃላፊነት የተጣለበት ነው። 

በአጠቃላይ 336 አባላት ባሉት “የክልል ተወካዮች ጉባኤ”፤ እያንዳንዱ ክልል እና የከተማ አስተዳደር በ14 ተወካዮች፣ የፌደራል መንግስት ደግሞ በ15 ተወካዮች ይወከላሉ። ለትላንት ሐሙስ ነሐሴ 14፤ 2018 ጠዋት የተጠራው “የክልል ተወካዮች ጉባኤ”፤ ምዕላተ ጉባኤው ባለሟሟላቱ ስብሰባውን ወዲያውኑ ማካሄድ አልቻለም። 

ከምሳ ሰዓት መልስ እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ ስብሰባው ያካሄደው “የክልል ተወካዮች ጉባኤ”፤ “ቅርቃር” ውስጥ በገባው በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ መወያየቱን ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚህ ስብስባ ላይ ከትግራይ በስተቀር የሁሉም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የአዲሰ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተገኝተዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገራቸው አንድ የጉባኤው አባል፤ ስብሰባው የተጠናቀቀው በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ላይ አስማሚ ሃሳብ የሚያዘጋጅ “አቀራራቢ ኮሚቴ” በማቋቋም እንደነበር ገልጸዋል። ኮሚቴው የተቋቋመው በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይን በተመለከተ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “ከአቅሜ በላይ ነው” በማለቱ ምክንያት እንደሆነም አስረድተዋል። 

የሁሉም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እንዲካተቱበት በተደረገው በዚህ አቀራራቢ ኮሚቴ ውስጥ የትግራይ ክልል በሶስት ተወካዮች እንዲወከል ተደርጓል። በኮሚቴው ውስጥ 5 ከሃይማኖት ተቋማት፣ 6 ከሃገር ሽማግሌዎች፣ 3 ከፖለቲካ ፖርቲዎች ምክር ቤት፣ 1 ከመምህራን ማህበር እንዲሁም 1 ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የመጡ ተወካዮችም ተካትተዋል።

ይህ ኮሚቴ ከትላንት በስቲያ በኦሮሚያ ክልል ተመካካሪዎች የቀረበውን አቤቱታ በመመልከት፤ አቀራራቢ የሚባል ሀሳብ እንዲያዘጋጅ ከስምምነት ላይ መደረሱን “በክልል ተወካዮች ጉባኤ” ላይ የተሳተፉት ተመካካሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ኮሚቴው 10 አባላት ካሉባቸው ጀምሮ እስከ 500 ተሳታፊዎች ድረስ በያዙ ቡድኖች የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን፤ ከቃለ ጉባኤዎችን መርምሮ አስማሚ የሆነ ሀሳብ እንዲያቀርብ መወሰኑንም ገልጸዋል።

“አቀራራቢ ኮሚቴው” በዛሬው ዕለት የደረሰበትን የተጠቃለለ አስማሚ ሀሳብ እንዲያቀርብ ቀነ ቀጠሮ ቢያዝለትም፤ ኮሚቴው መቋቋሙ በራሱ በአማራ ክልል ተወካዮች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። የአማራ ክልል ተወካዮች ይህንን ተቃውሟቸውን ያሰሙት ትላንት ሐሙስ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጋር በተገኙበት ባካሄዱት ውይይት ነው። 

በዛሬው ስብሰባ ላይ የተወያዩ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአማራ ክልል ተወካይ፤ ኮሚቴውን ያቋቋመው “የክልል ተወካዮች ጉባኤ”  የተጠራበት አግባብ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል። “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” የተጠራው “ስምምነት በተደረሰበት ጉዳይ ላይ ነው” የሚሉት እኚህ ተወካይ፤ ይህ አካሄድ ጉዳዩ “ወደ ኋላ እንዲመለስ ፍላጎት መኖሩን” እንደሚያሳይ እና ድርጊቱም እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። 

በትላንቱ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ውሎ፤ ከአማራ ክልል ተወካዮች በተጨማሪ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ተመካካሪዎች በተናጠል ውይይት ማድረጋቸውን አንድ ተሳታፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሌሎች ተመካካሪዎች የሀገራዊ ምክክሩ ወጥ ሰነድ ይቀርብ እንደሆነ በሚል እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ድረስ ሲጠብቁ መዋላቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)