በመጠናቀቅ ላይ ባለው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ 476 ምክረ ሃሳቦች መቅረባቸው ተገለጸ  

በቀጣዮቹ ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ፤ በስምንት ዋነኛ መወያያ አጀንዳዎች ስር በአጠቃላይ 476 ምክረ ሃሳቦች መቅረባቸው ይፋ ተደረገ። የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ከተጠቃለሉ እና ከተጣጠሙ በኋላ የተዘጋጀውን አንድ ወጥ ሰነድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነገ አርብ አሊያም ከነገ ወዲያ ቅዳሜ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።

በ90 ንዑሳን አጀንዳዎች እና በ225 መሪ ጥያቄዎች ላይ ተመስርተው የተዘጋጁት 476 ምክረ ሃሳቦች መቅረባቸው ይፋ የተደረገው፤ በትላንትናው ዕለት በነበረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ውሎ ላይ ነው። በዚሁ የጉባኤ ውሎ ከየስራ ቡድኑ የተወከሉ 120 ተመካካሪዎችን ያካተተው የአጀንዳ አቀናጅ ቡድን፤ የተቀናጁ ምክረ ሐሳቦችን ለየስራ ቡድኖቹ አቅርቧል። 

የስራ ቡድኖቹ በየራሳቸው አጀንዳዎች ላይ የመጨረሻ ግብዓት ከሰጡ በኋላ ምክረ ሃሳቦቹ በመጨረሻው ሰነድ ላይ ተጠናቅረው እንዲቀርቡ ይህንኑ ወደሚሰራው ቡድን መርተዋቸዋል። የተጠቃለሉ ምክረ ሃሳቦችን የያዘው ሰነድ፤ በዛሬው ዕለት በአንድ አዳራሽ ለተሰበሰቡ አራት ሺህ ተመካካሪዎች ይቀርባል ተብሎ ቢጠበቅም እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ ይኸው አለመከናወኑን የኮሚሽኑ ምንጮች ገልጸዋል። 

በትላንቱ የጉባኤ ውሎ በተለይም በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ላይ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ያደመጡ እና በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲወያዩ የነበሩ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ቅሬታ ሲያሰሙ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። ተወካዮቹ በሻይ እና በምሳ እረፍት ወቅት በቡድን በመሆን ቅሬታ ሲያሰሙ የተስተዋሉ ሲሆን ከአንዳንድ ኮሚሽነሮች ጋርም ለረጅም ሰዓታት በመነጋገር ቅሬታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

የተመካካሪዎቹ የቅሬታ መነሻ “አዲስ አበባ የፌደራል ተጠሪ ትሁን” በሚለው ንዑስ አጀንዳ ላይ እንደሆነ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ አጣርቷል። ትናንት በተነበበው የተጠናቀረ አጀንዳ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነት ለፌደራል መንግስት ሆኖ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር እንድትሆን የሚል ምክረ ሃሳብ መቅረቡን ዘጋቢያችን በስፍራው ሆኖ ተከታትሏል። 

በተጨማሪም በኢፌዲሪ ህገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ያለው “ልዩ ጥቅም” የሚለው አገላለጽ ተስተካክሎ “የጋራ ጥቅም” በሚል እንዲካተት ምክረ ሃሳብ ቀርቧል። በ1987 ዓ.ም የጸደቀው ህገ መንግስት አንቀጽ 49፣ ንዑስ አንቀጽ 5 “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” ሲል ደንግጓል።

“አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆን አለባት” ከሚለው የምክክር አጀንዳ ጋር በተያያዘ ሁለት አማራጭ ምክረ ሃሳቦች ተነስተዋል። የመጀመሪያው አማራጭ “ሁሉም ክልሎች የራሳቸውን ርዕሰ ከተማ መምረጥ እንደሚችሉ” በህገ መንግስቱ ላይ እንዲሰፍር የሚጠይቅ ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ በመሆኗ ከክልሉ ጋር የሚኖራት ግንኙነት በህግ ሊደነገግ ይገባል” የሚል ነው። 

የፌደራል ከተሞችን ጉዳይ በመያዝ ሲመካከር በቆየው የስራ ቡድን ስምምነት ተደርሶበት ለሁሉም ቡድኖች የቀረበው ይህ ምክረ ሃሳብ፤ በኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ማስነሳቱን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ታዝቧል። በምክክሩ “በልዩነት የተያዙ” ወይም “ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች” ወደፊት በምን መልኩ መፍትሔ እንደሚያገኙ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኩል እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ በአመካካሪነት ሲሳተፉ የቆዩ ግለሰብ “ሙሉ በሙሉ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች [ሲኖሩ]፤ አማራጮችን በማጥበብ እና ያሉትን ልዩነቶች በምክንያት (justification) አስደግፎ የማቅረብ ስራ ተከናውኗል” ሲሉ ሂደቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዚህ ሂደት የተበታተኑ ምክረ ሃሳቦች ወጥነት እንዲኖራቸው እና ተቀራራቢ ሃሳቦች ወደ አንድ እንዲመጡ መደረጉንም ገልጸዋል።

ይህ አካሄድ የሃሳቦችን ፍሬ ነገር ሳይነካ፤ አገላለጻቸውን እና አጻጻፋቸውን የማስተካከል ስራን ያካተተ እንደሆነ አመካካሪው አመልክተዋል። በጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ሲኖሩም ተሳታፊዎቹ አማራጮችን ለማጥበብ ጥረት እንደሚያደርጉ እና በዚህም መሰረት የልዩነት ሃሳቦች ወደ አንድ ወይም ሁለት አማራጮች ዝቅ እንዲሉ ተደርገው እንዲቀርቡ መደረጉን አመካካሪው አብራርተዋል። 

በመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ ላይ ሲወያዩ የቆዩ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ተመካካሪ፤ ምክረ ሃሳቦቹ በንባብ ቢደመጡም የጋራ መግባባት (consensus) ላይ ለመደረሱ የተቀመጠው መመዘኛ “ግልጽ አለመሆኑን” በመጥቀስ ተችተዋል። እኚሁ ተመካካሪ ልዩነቶች እንዴት እንደሚስተናገዱ “በቂ ማብራሪያ አልተሰጠም” ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በሀገራዊ ጉባኤው አመካካሪ የነበሩት ግለሰብ፤ የምክክሩ ሂደት “ከልሂቃን ድርድር ይልቅ የማህበረሰብ ምክክር ላይ ያተኮረ ነበር” ባይ ናቸው። “የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች የህዝቡን ፍላጎት የሚያሳዩ በመሆናቸው፤ መንግስት በቀረቡት አማራጮች ላይ ተመስርቶ የህግ እና የህገ መንግስት ማሻሻያዎችን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል” ሲሉም ቀጣዩ ሂደት ምን እንደሚሆን ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)