የ“አዲስ ስታንዳርድ” ዋና አዘጋጅ ታስሮ መለቀቁን እና የድርጅቱ ንብረቶች በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን አሳታሚው አስታወቀ

የ“አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር፤ ባለፈው ቅዳሜ “በጸጥታ አባላት” ተይዞ ከአንድ ቀን በኋላ መለቀቁን አሳታሚ ድርጅቱ አስታወቀ። ይህ ድርጊት በተፈጸመ በማግስቱ “የጸጥታ እና የደህንነት አባላት” ወደ “አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ በመግባት፤ መገናኛ ብዙሃኑ ለስራ የሚገለገልባቸውን ንብረቶች ይዘው መሄዳቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 30፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው። ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ የደረሱ ክስተቶችን በዝርዝር የያዘው መግለጫው፤ ከዋና አዘጋጁ እስር እና ከንብረቶች መወሰድ በተጨማሪ ድርጅቱ ላለፉት 16 ዓመታት በቢሮነት ሲጠቀምበት ከቆየው ህንጻ በሶስት ቀናት ውስጥ “በግዴታ እንዲለቅቅ” ቀነ ገደብ እንደተሰጠው አመልክቷል።

ድርጅቱን “ኢላማ ካደረጉ” ተከታታይ እርምጃዎች መካከል በቀዳሚነት የተፈጸመው የዋና አዘጋጁ ዮናስ እስር ነው። ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 25 “በጸጥታ አባላት” የተያዘው ዮናስ፣ ከ24 ሰዓት ገደማ ቆይታ በኋላ መለቀቁን አሳታሚ ድርጅቱ ገልጿል። ዋና አዘጋጁ ታስሮ በቆየበት ጊዜ “አካላዊ ጥቃት” እና “የተራዘመ ምርመራ” እንደተደረገበትም የድርጅቱ መግለጫ አክሏል።

በዋና አዘጋጁ ላይ ተፈጸመ የተባለው “እገታ”፤ በ“አዲስ ስታንዳርድ” ላይ ሲተገበር የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም። የመገናኛ ብዙሃኑ ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነው ሚሊዮን በየነ ባለፈው ሚያዝያ ወር “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች” ከቢሮው ከተወሰደ በኋላ የደረሰበት ሳይታወቅ ለ20 ቀናት ታስሮ ቆይቷል።

ሚሊዮን ታስሮ የቆየው በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ “ኢ-መደበኛ” ማቆያ ስፍራዎች እንደነበር መገለጹ ይታወሳል። ወደ “አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ በመግባት ጋዜጠኛውን የያዙት ግለሰቦች፤ “ስልኩን ሲቀበሉት” እና “ላፕቶፑን በእጁ ይዞ እንዲሄድ” ሲያደርጉት በደህንነት ካሜራ (CCTV) መቀረጻቸውን አሳታሚ ድርጅቱ በፎቶዎች የተደገፈ ማስረጃ በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር።

ይህ ድርጊት ከተፈጸመ ከሶስት ወራት በኋላ ባለፈው እሁድ ሐምሌ 26፤ “በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ናቸው” የተባሉ “የጸጥታ እና የደህንነት አባላት” በተመሳሳይ መልኩ “ያለ ህጋዊ ፍቃድ” ወደ መገናኛ ብዙሃኑ ቢሮ በመግባት ንብረቶችን መውሰዳቸውን አሳታሚ ድርጅቱ አስታውቋል። “የጸጥታ እና የደህንነት” አባላቱ ከወሰዷቸው ንብረቶች መካከል ቪዲዮ ካሜራዎች፣ ማይክሮፎኖች፣ የድምጽ እና የቪድዮ ማቀናበሪያ መሳሪያዎች፣ ትራይፖዶች እና ባትሪዎች እንደሚገኙበት ድርጅቱ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል።



ከእነዚህ ንብረቶች በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃኑ ዜና እና መልቲሚዲያ ክፍል ለዕለታዊ ስራዎቹ የሚገለገልባቸው ሌሎች የብሮድካስት መሳሪያዎች መወሰዳቸውን ድርጅቱ ገልጿል። ድርጅቱ በስተኋላ ላይ ባደረገው ማጣራት፤ በስቱዲዮ ውስጥ የቀሩ የመብራት ዕቃዎች፣ የማይክራፎን መያዣዎች፣ የኃይል አቅርቦት መሳሪያዎች እና ሌሎች ተያያዥ የፕሮዳክሽን መሳሪያዎች ላይ “ሆን ተብሎ የማበላሸት” ተግባር መፈጸሙን እንደደረሰበትም አብራርቷል።

በሚያዝያ 2017 ዓ.ም. ፖሊስ በ“አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ ባደረገው ብርበራ፤ መገናኛ ብዙሃኑ የሚጠቀሙባቸው የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች በተመሳሳይ መልኩ መወሰዳቸውን ድርጅቱ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ፖሊስ በብርበራው የወሰዳቸው ላፕቶፖች፣ ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ የሞባይል ስልኮች፣ ፍላሽ ዲስኮች እና ሲፒዩዎች ከቀናት በኋላ ቢመለሱም፤ የድርጅቱ የአይቲ ባለሙያዎች በንብረቶቹ ላይ ባደረጉት “ሙያዊ ፍተሻ” በውስጣቸው “የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌሮች (malware) መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ” ማግኘታቸውን በዚሁ መግለጫ ይፋ ተደርጓል።

ባለፉት ዓመታት ይህን መሰል ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙት የቆየው “አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን፤ ከምስረታው ጀምሮ ሲጠቀምበት ከቆየው ቢሮው “በግዴታ እንዲለቅቅ” የሚጠይቅ ማሳሰቢያ እንደደረሰው በዛሬው መግለጫው ላይ አስፍሯል። መገናኛ ብዙሃኑ ሲገለገልበት ከቆየው ቢሮው እንዲለቀቅ የተሰጠው ቀነ ገደብ ሶስት ቀናት ብቻ እንደሆኑም በመግለጫው ጠቅሷል።

መገናኛ ብዙሃኑ የመልቲሚዲያ ስቱዲዮ ጭምር የገነበባት ቢሮው የሚገኘው፤ በአዲስ አበባ ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኝ ህንጻ ውስጥ ነው። የህንጻው ባለቤት “አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮውን እንዲለቅቅ ማሳሰቢያ የሰጡት፤ ይህንን እንዲያደርጉ “በፖሊስ ከተገደዱ” በኋላ መሆኑን የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ድርጅት መግለጫ አትቷል።

የመልቀቂያ ቀነ ገደቡ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከህንጻው አስተዳደር ጋር የገባውን ውል የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ ድርጅቱ ይፋዊ ቅሬታ አቅርቧል። ድርጅቱ ይህንን ለማስቀየር “ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ጀምሬያለሁ” ብሏል በመግለጫው።

የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ድርጅት፤ የ“አዲስ ስታንዳርድ” የምዝገባ ምስክር ወረቀት መሰረዝን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱ አይዘነጋም። የመገናኛ ብዙሃኑ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ መሰረዙን ያስታወቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ነው።

ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ይህን እርምጃ የወሰደው፤ “አዲስ ስታንዳርድ” “የሚዲያ ስነ-ምግባርን፣ የኢትዮጵያን ህጎች እና የሀገርንና የህዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ አሰራጭቷል” በሚል ምክንያት ነበር። የቀረቡበትን ውንጀላዎች ውድቅ ያደረገው የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ድርጅት፤ ይህንኑ በመቃወም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ጉዳዩን እየተከታተለ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)