በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ “የጽምጽ ውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት” ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ተሳታፊዎች ገለጹ 

ሰላሳ አራተኛ ቀኑን በያዘው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ በአጀንዳዎች ላይ ውሳኔ እየተሰጠ ያለው “የድምጽ አሰጣጥ ስርዓትን” በተከተለ አግባብ አለመሆኑን ሶስት የጉባኤው ተሳታፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በጉባኤው ላይ በማመካከር እና በታዛቢነት እየተሳተፉ ያሉ ሁለት ግለሰቦችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጀው ሰነድ በአጀንዳዎች ላይ ውሳኔ የሚደረሰው በየደረጃው ያሉ ተሳታፊዎች ከ70 እስከ 75 በመቶ ድጋፍ ሲሰጡ እንደሆነ ያስቀምጣል። ኮሚሽኑ የዘረጋው ይህ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ግን እስካሁን በየደረጃው ባሉ የቡድን ምክክሮች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እየተመካከሩ የሚገኙ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የፌደራል ከተሞችን በሚመለከተው አጀንዳ ስር ሲመካከሩ የቆዩት የወለኔ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይ ኮሎኔል አለማየሁ ኃይሌ፤ እርሳቸው በነበሩበት ቡድን የጸደቀው ሃሳብ በድምጽ ብልጫ ሳይሆን “በመግባባት” እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፌደራል ከተሞችን የሚመለከተው አጀንዳ፤ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከተጀመረበት ሐምሌ 8፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ውዝግብ እና አለመግባባት ከፈጠሩ ጉዳዮች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።

በዚህ አጀንዳ ስር የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ጉዳይ ለምክክር ቢቀርብም፤ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ነው። እርሳቸው በነበሩበት ቡድን “አዲስ አበባ የፌደራል መቀመጫ ትሁን” የሚለው ሃሳብ “የአብላጫውን ድጋፍ ማግኘቱን” የገለጹት ኮሎኔል አለማየሁ፤ እርሳቸውን ጨምሮ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆን አለባት” ያሉ ተመካካሪዎች ሃሳብ “በልዩነት መያዙን” አስረድተዋል ። 

በቡድናቸው የጸደቀው ሃሳብ “በድምጽ አሰጣጥ ስርዓት የተከናወነ መሆኑን” የተጠየቁት ኮሎኔል አለማየሁ፤ “ድምጽ ብልጫ አልተደረገም። መግባባቱ እጅ በማውጣት ሳይሆን ከአጠቃላይ ሁኔታው እና ከፊርማዎች አንጻር ግምት በመውሰድ የተደረገ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ክልሎችን ቅርቃር ውስጥ የሚከቱ ጉዳዮች ካሉ የክልል ተወካዮች ጉባኤ እንደሚመለከተው ያስታወሱት፤ ተመካካሪው “የድምጽ አሰጣጡ የሚኖረው ይሄ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ይመስለኛል” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ከሁሉም ክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከፌደራል ተቋማት የተውጣጡ 336 አባላት ያሉት የክልል ተወካዮች ጉባኤ፤ አከራካሪ ጉዳዮችን በልዩ ሁኔታ እንዲወስን ወይም እንዲያጸድቅ ታስቦ የተቋቋመ ነው። ይህ ጉባኤ ከተቋቋመ ሁለት ሳምንት ቢሞላውም፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የዘረጋው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓቱ ባለመተግበሩ ምክንያት እስካሁን ወደ ስራ እንዳልገባ መገንዘብ ተችሏል።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉን፤ በመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ ላይ የተሳተፉ እና ተመካካሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “አስተያየትም ሆነ ሌላ ውይይት ሳይደረግ ‘ተስማምተናል’ ተብሎ ቀጥታ የሃይማኖት አባቶች ገብተው ወደ ምርቃት ነው የተሄደው” ሲሉ ተመካካሪው ሂደቱን ተችተዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ እኚሁ ተመካካሪ፤ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ ቃለ ጉባኤ ላይ ፊርማቸውን አለማኖራቸውን አመልክተዋል። “እኔ ሲጀመር አስር አባላት ካሉት ቡድን በኋላ አልፈረምኩም። በ50ም፣ በ250ም ውሳኔ አልስማማም” ሲሉ በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ የስራ ቡድኖች ያለፉበትን ሂደት አስረድተዋል። 

በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ የተሳተፉ ሌላ ተመካካሪም፤ እርሳቸው በነበሩበት ቡድን ወደ ድምጽ አሰጣጥ አለመገባቱን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። “በድምጽ ብልጫ ማሸነፍ ቅሬታ ሊፈጥር ስለሚችል፣ ኮሚሽኑ ውሳኔ ሰጪ ሳይሆን ሃሳብ አዋጪ በመሆኑ፤ መንግስት ለራሱ ሲል የጠራው በመሆኑ ‘ይተገብረዋል’ የሚል መግባባት ተፈጥሯል” ሲሉ የነበረውን ሂደት ገልጸዋል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የታዛቢነት ሚናቸውን እየተወጡ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ፤ የድምጽ አሰጣጥ ስርዓቱ ተግባራዊ ያልሆነበትን ምክንያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። አቶ ተስፋዬ “ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ ድምጽ አያስፈልግም። ስለዚህ በተቻለ መጠን ጥረት እየተደረገ ያለው ሁሉም ነገር በስምምነት (consensus) እንዲያልቅ ነው” ብለዋል። 

“እስካሁን ቅርቃር ውስጥ ሊከትቱ የሚችሉ ጉዳዮች አልገጠሙም። ይህ ማለት ግን የማያግባቡ ጽንፍ የወጡ አጀንዳዎች የሉም ማለት አይደለም። ነገር ግን እነዚያን ጽንፍ የሆኑ አጀንዳዎች የባለሙያዎች ቡድን ሁለቱንም ወገኖች በማግባባት ወደ መሃል እያመጣቸው ስለሆነ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ አድርጓል” ሲሉም የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር በሂደቱ የታዘቡትን አስረድተዋል።

በምክክር ጉባኤው ወደ ድምጽ ከማምራት ይልቅ ሁለት ጽንፍ የያዙ አካላትን ሊያስታርቁ የሚችሉ አማካይ ሃሳቦችን ማምጣት እንደሚመረጥ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ “ወደ ድምጽ መሄድ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መዘዙ ጥሩ ላይሆን ይችላል” ብለዋል። “ድምጽ መስጠት (voting) ከመጣ አንዳንዴ ያልተፈለገ ውጤት ሊያመጣ ይችላል” ሲሉም አክለዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ተልዕኮ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ መሆኑን የጠቀሱት የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር፤ “የሚቀርቡት ምክረ ሃሳቦች አንዳንዶቹ ወደ ህግ፣ አንዳንዶቹ ወደ ፖሊሲ፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ህገ መንግስት ማሻሻያ ሊያመሩ ይችላሉ። ይህ በሂደት ታይቶ መጨረሻ ላይ የሚታወቅ ይሆናል። ወደ ህዝበ ውሳኔ የሚሄዱም ይኖራሉ” ሲሉ ከምክክር ጉባኤው የሚጠበቀውን ውጤት አስገንዝበዋል። 

በምክክር ጉባኤው ሁሉንም የውሳኔ ሂደቶች አልፈው ለጠቅላላ ጉባኤ ከቀረቡ በኋላ “ጠንካራ ተቃውሞ” የሚያጋጥማቸው አጀንዳዎች፤ ወደ ህዝበ ውሳኔ “ሊመሩ” እንደሚችሉ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ላይ ተቀምጧል። ይኸው ሰነድ በምክክር ጉባኤው“ያልተፈቱ ጉዳዮች” በህዝበ ውሳኔ እንዲፈቱ ተሳታፊዎች ከጠየቁ፤ ይህ አማራጭ ተግባራዊ እንደሚደረግም ይገልጻል።

በዚሁ ሰነድ ላይ ለምክክር በቀረበ አጀንዳ ላይ 75 በመቶ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ድጋፉ ወደ 70 በመቶ ዝቅ እንዲል እንደሚደረግ፤ ይህም ካልተሳካ ግን ጉዳዩ ውድቅ እንደሚሆን ተመልክቷል። በመቶኛ ተሰልቶ የተቀመጠው የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉን በተመለከተ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የጉባኤው አመካካሪ፤ “ለጊዜው በሰነዱ መሰረት ድምጽ እየሰጡ መሄድ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም” ብለዋል።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ይህ የተደረገው “አብዛኛው ጉዳይ በስምምነት እየሄደ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ አመካካሪው ገልጸዋል። በአጀንዳዎች ላይ የተንጸባረቁ “ልዩነቶች በቃለ ጉባኤ የተያዙ” መሆናቸውን የሚጠቅሱት እኚሁ አመካካሪ፤ “የሚጣል ሃሳብ የለም” ሲሉ ይህን በተመለከተ ስጋት ለገባቸው ወገኖች ማረጋገጫ ለመስጠት ሞክረዋል። በአጀንዳዎች ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በድምጽ አሰጣጥ ማሳለፍ “ሂደቱን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው” የሚሞግቱት አመካካሪው፤ ስምምነት ላይ ባልተደረሳባቸው “ጥቂት ጉዳዮች” ወደ ድምጽ ከመግባት ይልቅ “ሁሉንም ሃሳቦች አካትቶ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ የተሻለ አካሄድ ነው” ባይ ናቸው።

በይፋ ከተከፈተ አንድ ወር በተሻገረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ ለአንድ ሳምንት ያህል ሲከናወን የቆየው በአጀንዳዎች ላይ የተሰጡት ሃሳቦችን የማናበብ እና ወጥ የሆነ ምክረ ሃሳብ የማደራጀት ስራ ትላንት ሰኞ ነሐሴ 11፤ 2018 ዓ.ም መጠናቀቁ ተገልጿል። ይህን ስራ ሲያከናውኑ የቆዩት 120 የሚሆኑ የጋራ ማረጋገጫ ቡድኖች ናቸው።

በትላንትናው ዕለት ከሰዓት ከ10 ሰዓት ጀምሮ፤ ሁሉም ተመካካሪዎች በየቡድኖቻቸው በመሆን ተጠናቅሮ በቀረበው አጀንዳ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል። የአጀንዳ አደራጆች የመጨረሻ ምክረ ሃሳቦችን ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ለተመካካሪዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ያለፉትን ቀናት የምክክር ጉባኤውን ውሎዎች በተመለከተ በትላንትናው ዕለት መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ፤ የተጠናቀሩት ምክረ ሃሳቦች በነገው ዕለት ለ4 ሺህ ጉባኤተኞች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል። ጉባኤው የሚቀርቡለትን አጀንዳዎች ያጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ እስካሁን ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ዕጣ ፈንታ ዙሪያ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)