የወላይታ ዞን አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወሰነ

በደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ፤ በወላይታ ዞን የፓርቲው አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ከፓርቲው እና ከመንግስት ስራ ኃላፊነታቸው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 14፤ 2012 ጀምሮ እንዲነሱ መወሰኑን አስታወቀ። አስተባባሪ ኮሚቴው ውሳኔውን ይፋ ያደረገው ዛሬ ቅዳሜ ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው።

መግለጫው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተባሉትን ኃላፊዎች በስም ባይዘረዝርም በወላይታ ዞን በአመራርነት ላይ ያሉ መሆናቸውን በደፈናው ገልጿል። የወላይታ ዞን አመራሮች “ለውጡን በጉልበት ለመቀልበስ የተለያዩ ታክቲኮችን በመንደፍ፥ በክልል የመደራጀት ጥያቄ አመላለስ ለማወሳሰብ አቅደዉ በመፈፀም፣ በዞኑ ያለመረጋጋትና የንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነዋል” ሲል አስተባባሪ ኮሚቴው ወንጅሏል።

“የወላይታ ዞንን እንዲመሩ ኃላፊነት የወሰዱ አመራሮች ከፓርቲዉ ዲስፒሊንና ከተሰጣቸው ህዝባዊና መንግስታዊ ኃላፊነት በተቃራኒ በመቆም የህዝቡን ጥያቄ ሽፋን በማድረግ ለዉጡን ለማደናቀፍ በግልፅና በህቡዕ ተደራጅቶ ከሚንቀሳቀሱ የዉስጥ እና የውጪ ኃይሎች ጋር እየሰሩ እንዳሉ ተረጋግጧል” ሲል ኮሚቴው በዛሬ መግለጫው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)