በተስፋለም ወልደየስ
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ዋና ጸሀፊ የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ በሕገ መንግስት እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ተከሰሱ። አቶ ደጀኔ ክስ የቀረበባቸው ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 26፤ 2012 ባስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ነው።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአቶ ደጀኔ እና አቶ መስተዋርድ ተማም በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ባቀረበው ክስ፤ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ከሚገኙ እና ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን እንደነበር ጠቅሷል። ሁለቱ ተከሳሾች “በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማ ወይም ህገ ወጥ በማናቸውም መንገድ በሕገ መንግስቱ የተቋቋመውን ስርዓት ለማፍረስ በማሰብ ከሰኔ 2012 ዓ.ም. በኋላ መንግስት የስልጣን ዘመኑ የሚጠናቀቅ በመሆኑ መንግስት ሆኖ መቀጠል ስለማይችል የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ግፊት ሲያደርጉ ነበር” ሲል አቃቤ ህግ በክስ ቻርጁ ላይ አስፍሯል።
ተከሳሾቹ “ ‘የኦሮሞ ህዝብ በአመጽ በአንድ ላይ በመነሳት የሀገር ባለቤትነቱን ማረጋገጥ አለበት፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የምኒልክ እና ሌሎች ተመሳሳይ ሀውልቶች መፍረስ አለባቸው፣ የኦሮሞ ቄሮዎች የሌሎች ብሔር ተወላጆችን ንብረት ማቃጠል አለባቸው፣ በቄሮ ደም ቤተመንግስት የገባውን ኃይል በቄሮ ትግል ማስወገድ አለብን’ በማለት ህዝብን ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል” ሲል የክስ ሰነዱ አትቷል። ተከሳሾቹ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ያሰቡትን አላማ ለማሳካት መንቀሳቀሳቸውንም አቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።
የሃጫሉ የቀብር ስነ ስርዓት በአምቦ እንዲከናወን አስክሬኑ በመሸኘት ላይ እያለ በአንደኛ ተከሳሽነት በክስ መዝገቡ የሰፈሩት አቶ ደጀኔ፤ በተመሳሳይ የምርመራ መዝገብ ተጠርጣሪ ከሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በስልክ ትዕዛዝ መቀበላቸውን የክስ ሰነዱ ያመለክታል። የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ለሌላኛው የፓርቲያቸው አመራራ አቶ ደጀኔ ሰጡት የተባለው ትዕዛዝ “ወጣቶችን አደራጅተው የሃጫሉ አስክሬን ከኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን፣ ቡራዩ ከተማ፣ ኬላ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ እንዳያልፍ እና ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ እንዲያደርጉ” የሚያሳስብ እንደሆነ የክስ ሰነዱ ያብራራል።
አቶ ደጀኔ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው በቡራዩ ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርካታ ወጣቶችን በማስተባበር መንገድ በማዘጋት እና ከሟች ቤተሰብ ፍቃድ ውጪ የሃጫሉን አስክሬን በማስገደድ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ማድረጋቸውን በክስ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። ተከሳሾቹ ከአቶ በቀለ እና ከሌሎችም ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ያስተባበሯቸው ወጣቶች ጉዳት ለማድረስ የሚያስችሉ የተለያዩ መሳሪያዎችን የያዙ እንደነበርም ክሱ አመልክቷል።
የኦፌኮ ምክትል ዋና ጸሀፊ ድምጻዊ ሃጫሉ በተገደለበት ሰኔ 22፤ 2012 ለሊት፤ አምስት ሰዓት ከ10 ደቂቃ ገደማ በስልክ ሰጡት የተባለው ትዕዛዝም በክስ ሰነዱ ተጠቅሶባቸዋል። አቶ ደጀኔ የስልክ ትዕዛዙን ያስተላለፉት በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ደምበል ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ለነበረ ግብረአበራቸው መሆኑን አቃቤ ህግ በክሱ አስፍሯል።
እስካሁንም በቁጥጥር ስር አለመዋሉ በሰነዱ የተገለጸው ይህ ግለሰብ፤ የሃጫሉን ግድያ በመቃወም “ወደ መንገድ መውጣታቸውን እና መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ የመጨረሻ ትግል እንደሚያደርጉ” ለአንደኛ ተከሳሽ ነግሯቸዋል ተብሏል። በስልክ ልውውጡ ወቅት አቶ ደጀኔ ግለሰቡን “በርቱ” ማለታቸውን እና “ሀገሪቷ የቄሮ በመሆኗ እንደፈለጉ እንዲያደርጉ” ትዕዛዝ መስጠታቸውን አቃቤ ህግ በክሱ አትቷል።
ተከሳሹ ከድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ ማግስት፤ ሰኔ 23፤ 2012፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ አካባቢ ለነበረ ግብረአበራቸውም ሌላ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውም በክስ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። ለጊዜው ስሙ አለመታወቁ በሰነዱ ለተጠቀሰው ግብረአበር የተሰጠው ትዕዛዝ “ወጣቶች ተቀናጅተው በየአካባቢው የመንግስትን መዋቅር እንዲቆጣጠሩ” የሚል እንደነበር አቃቤ ህግ በክሱ ገልጿል።
በተከሳሾቹ በተነሳሳው “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን የመናድ ተግባር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን፣ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ የተለያዩ ንብረቶች መውደማቸውን የአቃቤ ህግ ክስ ዘርዝሯል። አቃቤ ህግ በዚህ የወንጀል ተግባር ምክንያት ተነሳ ባለው ግጭት፤ በቡራዩ ከተማ የ2 ሰዎች እና በአዲስ አበበ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የስድስት ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ብሏል።
እነ አቶ ደጀኔ በተከሰሱበት ወንጀል “በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ቀውስ የደረሰ በመሆኑ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ በሚደረግ ወንጀል ተከሰዋል”
– የአቃቤ ህግ የክስ ሰነድ
አቶ ደጀኔ እና አቶ መስተዋርድ በተከሰሱበት ወንጀል “በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ቀውስ የደረሰ በመሆኑ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ በሚደረግ ወንጀል ተከሰዋል” ሲል አቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ አስፍሯል። ተከሳሾቹ በክስ ሰነዱ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ህግ አንቀጽ 238 (2) “ወንጀሉ ሲፈጸም በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶ እንደሆነ፤ አድራጊው በዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት ይቀጣል” በማለት ይደነግጋል።
በዛሬው የችሎት ውሎ የቀረቡት ሁለቱ ተከሳሾች የክስ ቻርጁ እንደደረሳቸው ጠበቃቸው አቶ ቦሬሳ በየነ ገልጸዋል። “የክስ ቻርጁ የመጀመሪያ ቀን የደረሰን ስለሆነ ክሱን አይተን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገን ክርክር ለማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ ጠይቀናል” ሲሉ ጠበቃ ቦሬሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዛሬው ችሎት የተከሳሾች የዋስትና መብት በተመለከተም በችሎት የነበሩ ሶስት ጠበቆች ጥያቄ ማቅረባቸውንም አክለዋል።
የዋስትና መብት ጥያቄ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ጥያቄውን መርምሮ ተገቢውን ብይን ለመስጠት ለነገ በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 28፤ 2012 ቀጠሮ ሰጥቷል። በሐሙሱ ችሎት፤ በክሱ ላይ በጠበቆች በኩል ለሚቀርበው ምላሽ ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሚሰጥም የተከሳሾቹ ጠበቃ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)