ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ አላማጣ ከተማ በከባድ መሳሪያ ስትደበደብ ከተገደሉት መካከል፤ የ26 ዓመቷ ሜሮን ሰዋስው፣ የስምንት ዓመት ወንድ ልጇ ማርኮን ግርማ ህይወት እና ወንድሟ ተወከል ሰዋስው ይገኙበታል። የሜሮን የሁለት ዓመት ወንድ ልጅ በድብደባው ቢቆስልም በህይወት መትረፉን አባቱ ግርማ ሕይወት ነጋሽ ገልጸዋል።
ግርማ ሕይወት በከተማው ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ሲፈጸም ለስራ ጉዳይ ከአላማጣ ርቀዋል። ቤተሰቦቻቸው ግን ከጦርነቱ የተሻለ መከለያ ይሆናል ብለው ባመኑት በመኖሪያ ቤታቸው ነበሩ። ባለቤታቸውን ከልጃቸው ጋር በአንድ ቀን የተነጠቁት ገብረ ህይወት፤ “የሃይስኩል ፍቅሬ ነበረች፤ ታሪካችን በአጭሩ ተቀጨ” ሲሉ ጥልቅ ሀዘናቸውን ለዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል አጋርተዋል።
ወይዘሮ ሜሮን የተገደለችበት በአላማጣ ቀበሌ 04 አካባቢ የሚገኘው እና በተለምዶ “ኮንዶሚኒየም” ተብሎ የሚጠራው ሰፈር መስከረም 17፤ 2019፤ ኃይለኛ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ከተፈጸመባቸው የከተማዋ ክፍሎች አንዱ ነው። በዕለቱ በዚያው ሰፈር አምስት የመኖሪያ ቤቶች በከባድ መሳሪያ እንደተመቱ ሶስት የአይን እማኞች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግረዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 15፤ 2019 ይፋ ባወጣው የምርመራ ሪፖርት፤ በከባድ መሳሪያው ድብድባ ምክንያት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች አራት መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል። ከመስከረም 16 እስከ 18 ባሉት ሶስት ቀናት ውስጥ በአላማጣ ከተማ በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ድብደባ 14 ሰዎች መገደላቸውን እንዳረጋገጠ በሪፖርቱ አስፍሯል።
የከባድ መሳሪያ ድብደባው የተጸመው በመከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እንደሆነም የድርጅቱ የምርመራ ሪፖርት አመልክቷል። የአላማጣ ከተማ የከባድ መሳሪያ ዒላማ የሆነችው፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄን (አፋብን) ያሉበት ጥምረት፤ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ከመንግስት ኃይሎች ጋር ውጊያ ከጀመረ በኋላ ነው።
ጥምረቱ ሰባት አማጺያንን እንዳቀፈ ቢገለጽም በሶስቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተደረጉ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ከባድ ውጊያዎች የተሳተፉት፤ የህወሓት ኃይሎች፣ የአፋብን እና የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (ኡጉጉሞ) ታጣቂዎች ናቸው። በመስከረም ወር የተካሄዱት ውጊያዎች ግለት ቢለያይም፤ የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ሶስት የተለያዩ ግንባሮች ተፈጥረው ታይተዋል።
በአፋር በኩል የኡጉጉሞ ታጣቂዎች እና የህወሓት ኃይሎች በመጀመሪያዎቹ ቀናት በኪልበቲ ረሱ ዞን ውስጥ አብአላ፣ መጋሌ፣ ወሰማ እና ኤሬብቲን በመሳሰሉ አካባቢዎች ከመከላከያ ሰራዊት እና ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተዋግተዋል። ሁለቱ አማጽያን መስከረም 12፤ 2019 የአብአላ ወረዳን ተቆጣጥረው እንደነበር በዓለም ዙሪያ የሚደረጉ ግጭቶችን እየተከታተለ የሚሰንደው “አክሌድ” የተሰኘው ተቋም ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል።
በመስከረም ወር አጋማሽ በትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት የወልቃይት አካባቢ፤ የትግራይ ኃይሎች ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ውጊያ ያደረጉት ውጊያም ይጠቀሳል። በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን ውስጥ የሚገኙት አቀስታ፣ ጭላ፣ ሐሙሲት እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን እንጃፋት፣ ተኩለሽ እና ጊዳን በተለይ በመንግስት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የተካሄደባቸው አካባቢዎች ናቸው።
የህወሓት ኃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመሆን የተዋጉባቸው በትግራይ እና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙት የቆቦ – ጥሙጋ እና የዛታ – ሰቆጣ ግንባሮች ውጊያ የተጀመረው መስከረም 13 እንደነበር የ“አክሌድ” መረጃ ያሳያል። በአላማጣ እና በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች ውጊያ የተጀመረው፤ ከዚህ ክስተት አንድ ቀን አስቀድሞ ነበር።
ከመስከረም 12 ጀምሮ ባሉት ለሶስት ቀናት በተካሄደው በዚሁ ከባድ ውጊያ ጉዳት የደረሰባቸውን ከ420 በላይ ቁስለኞች በኮረም እና በአላማጣ ከተሞች የሚገኙ ሆስፒታሎች መቀበላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በወቅቱ አስታውቋል። ቁልፍ የወታደሮች፣ የምግብ እና የነዳጅ መተላለፊያ የሆነችውን የአላማጣ ከተማ ለመቆጣጠር የተደረገው ፍልሚያ፤ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ ዛሬ ይፋ የተደረገው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ውጤት አሳይቷል።
መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን መስከረም 18፤ 2019 አላማጣን ከመቆጣጠራቸው በፊት ለሶስት ቀናት ከተማዋን በከባድ መሳሪያ እንደደበደቡ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በሪፖርቱ አስፍሯል። የተቋሙ ምርመራ ከመስከረም 16 እስከ 18 በከተማው ላይ በተፈጸሙ አራት የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ላይ ያተኮረ ነው።
ወይዘሮ ሜሮን ሰዋስው ከልጇ እና ከወንድሟ ጋር ህይወቷን ያጣችበት አንደኛው የከባድ መሳሪያ ድብደባ፤ ጎረቤታቸው የነበሩ አራት ሰዎችንም እንደገደለ በምርመራው ውጤቱ ላይ ተመልክቷል። ኩምኺስ ካህሳይ እና የ14 ዓመት ልጃቸው ህሊና ኃይላይ፣ ለዙ ይርጋ እና የሶስት ዓመት ልጃቸው በተመሳሳይ ጥቃት የተገደሉ ሰለባዎች ናቸው።

በዚያን ዕለት ጥቃት የተፈጸመባቸው ሁለት ቤቶች፤ “የህወሓት ተዋጊዎች እንደነበሩባቸው” በነዋሪዎች ከተገለጸው ወርቅነሽ ሆቴል 150 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ነበሩ። በቤቶቹ ላይ የደረሱትን ጉዳቶች የሚያሳዩ አራት ቪዲዮዎችን የመረመረው፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የማስረጃ ላብራቶሪ ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጧል።
የደመራ በዓል በሚከበርበት መስከረም 16 ቀን “ንጉስ ሺሞይ” የተባለ መጠጥ ቤት በከባድ መሳሪያ ሲመታ፤ ቢያንስ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን በጥቃቱ የቆሰሉ የዓይን እማኝ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጸዋል። በሌላ የከተማዋ ክፍል በማግስቱ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት የ55 ዓመት ወይዘሮ ሲገደሉ ባለቤታቸው እና ሶስት ልጆቻቸው መቁሰላቸውን የአይን እማኞች ለድርጅቱ አስታውቀዋል።
ጥቃት የተፈጸመበት የከባድ መሳሪያ ተተኳሽ ስብርባሪዎች መከላከያ ሰራዊት ከሚጠቀምባቸው ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ መርማሪ እንዳረጋገጡ በዛሬው ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። ምርመራዎቹ በተከናወነባቸው ቀናት በአላማጣ ሆስፒታል ተረኛ የነበሩ የህክምና ባለሙያ፤ በሶስቱ ቀናት ወደ ህክምና ተቋም የመጡት አብዛኞቹ ተጎጂዎች “በከባድ መሳሪያ ፍንጥርጣሪ” ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ስማቸው ያልተገለጸው እኚሁ የህክምና ባለሙያ፤ ሁሉም ተጎጂዎች ሲቪሎች መሆናቸውን ለድርጅቱ ገልጸዋል። በአላማጣ ከተማ የተፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ፤ የከተማውን “80,000 ነዋሪዎች ሕይወት ችላ በማለት” ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተፈጸሙ መሆናቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰብአዊ መብቶች ቀጠናዊ ከፍተኛ ዳይሬክተር ያስሚን አህመድ መናገራቸው በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
“ሰፊ አካባቢዎችን የመምታት አቅም ያለውን መድፍ ህዝብ በተጨናነቀባቸው ሰፈሮች ውስጥ መጠቀም በሰላማዊ ሰዎች ላይ አስከፊ ጉዳት” እንደሚያስከትል የገለጹት ኃላፊዋ፤ “በዘፈቀደ የሚፈጸሙ ጥቃቶች” ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ የሚጥሱ በመሆናቸው “እንደ የጦር ወንጀል ሊመረመሩ ይገባል” ብለዋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምርመራ መሰረት በአላማጣ ላይ ድብደባ የተፈጸመው፤ ከከተማዋ በስተደቡብ በ13 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኝ ዋጃ እና ጥሙጋ ከተባለ አካባቢ ነበር። አንድ የአይን እማኝ መከላከያ ሰራዊት ከባድ መሳሪያዎች በዋጃ በተለይ አየር ማረፊያ ወደተባለው አካባቢ ሲያንቀሳቅስ መመልከታቸውን ለመርማሪዎቹ እንደገለጹ በሪፖርቱ ሰፍሯል።

አላማጣን ለመቆጣጠር ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ የተዋጋው የትግራይ የሰላም ኃይል፤ ከባድ መሳሪያ እንደታጠቀ ለቡድኑ ቅርበት ያላቸው ሁለት ግለሰቦች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግረዋል። የድርጅቱ የምርመራ ሪፖርት፤ በወቅቱ የህወሓት ኃይሎች ሚና እንደነበርም በዝርዝር አትቷል።
የህወሓት ኃይሎች “የታጠቋቸውን ከባድ መሳሪያዎች በውጊያ ወቅት ይተኩሱ እንደነበር” በምርመራ ሪፖርቱ የጠቀሰው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ሆኖም “በአላማጣ ከተማ ላይ የተፈጸመው ድብደባ ፈጽመዋል” ለማለት እንደማያምን ድምዳሜውን አስቀምጧል። በአላማጣ ከተማ የደረሰው የከባድ መሳሪያ ድብደባ፤ በወቅቱ በከተማው በነበሩ የህወሓት ኃይሎች “በራሳቸው በቀጥታ የተፈጸመ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እጅግ አነስተኛ ነው” ብሏል ድርጅቱ።
የተቋሙ መርማሪዎች ያነጋገሯቸው ስድስት ሰዎች በአላማጣ ከተማ የሚገኙ ሁሉም ሊባሉ የሚችሉ ትምህርት ቤቶች፤ ውጊያው ዳግም ከማገርሸቱ በፊት የህወሓት ተዋጊዎች የጦር ሰፈር ሆነው እንደነበር ገልጸዋል። ከመኖሪያ ሰፈሮች አቅራቢያ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች፤ ውጊያ ከተጀመረ በኋላ ከባድ መሳሪያ መተኮስን ጨምሮ የወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲደረግባቸው እንደነበር የምርመራ ውጤቱ አመልክቷል።

ለሪፖርቱ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሁሉም ነዋሪዎች፤ “ህወሓት ማስጠንቀቂያ እንዳልሰጠ እና ነዋሪዎቹ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ እንዳላዘዘ” ተናግረዋል። ህወሓት እንደ ጦር ሰፈር ከሚጠቀምበት “ብሩህ ተስፋ” የተባለ ትምህርት ቤት አካባቢ፣ “ሚሽነሪ ካምፕ” በተባለ ሰፈር በሚገኝ አንድ የመኖሪያ ቤት ላይ መስከረም 16 በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት፤ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ አራት መቁሰላቸውን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ላይ ሰፍሯል።
አንድ የአይን እማኝ በትምህርት ቤቱ የነበሩ አብዛኞቹ የህወሓት ታጣቂዎች፤ ከጥቃቱ ጥቂት ቀደም ብለው ለቅቀው መሄዳቸውን ተናግረዋል። ሌላ ምስክር በበኩላቸው ጥቃቱ ከመፈጸሙ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፤ ጥቂት የህወሓት ኃይሎች በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ጥበቃ ሲያደርጉ መመልከታቸውን አስረድተዋል።
አምነስቲ በትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ፣ ጥቃት ተፈጸመ በተባለበት ወቅት የህወሓት ታጣቂዎች በትምህርት ቤቱ ውስጥ መኖር አለመኖራቸውን በገለልተኝነት እንዳላረጋገጠ በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። ከአላማጣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚኖሩ ሌላ የከተማው ነዋሪ፤ ትምህርት ቤቱ መስከረም 12፤ 2019 በመከላከያ ሰራዊት ድሮን እንደተመታ ተናግረዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ የህወሓት ኃይሎች መስከረም 18 ለቀው ከመውጣታቸው በፊት፤ የአላማጣ ከተማን ለመከላከል የሚፈጽሙት የከባድ መሳሪያ ጥቃት ዋና መተኮሻ እንደነበር አምነስቲ ያነጋገራቸው እማኝ አስረድተዋል። እኚሁ እማኝ ትምህርት ቤቱ በድሮን ሲመታ ከፍተኛ ፍንዳታ መስማታቸውን እና በቦታው ተከማችቶ የነበረው ከባድ የጦር መሳሪያ ሲቃጠል መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የምርመራ ውጤቱ የቀረበለት ህወሓት ለአምነስቲ በጻፈው አራት ገጽ ደብዳቤ፤ የቀረቡበትን ውንጀላዎች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉን አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አስታውቋል። ፓርቲው የምርመራው የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች “በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ኃይሎቹ የተፈጸሙ ግፎችን ቢያረጋግጡም በትግራይ ኃይሎች ላይ የቀረበው ውንጀላ አሳስቦናል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የቀረቡበትን ክሶች “መሰረተ ቢስ” ያለው ህወሓት፤ “ተጠያቂነትን በተመለከተ ማንኛውም መደምደሚያ ላይ ከመደረሱ በፊት ተጨማሪ ገለልተኛ እና አጠቃላይ ምርመራ ሊደረግ ይገባል” የሚል አቋሙን አሳውቋል። በተመሳሳይ የምርመራ ውጤቱ የቀረበላቸው መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ የሰላም ኃይል ግን ምላሽ እንዳልሰጡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ አስፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































