አዲሱ የአዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የግዥ መመሪያ፤ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት የሰጣቸው ተጨማሪ ማበረታዎች የትኞቹ ናቸው? 

የአዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠይቁ የግንባታ ስራዎችን “አግባብነት ባለው የግዥ ዘዴ በማወዳደር” ለስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት መስጠት ተፈቀደላቸው። ይህን ፈቃድ የሰጠው ከህዳር 1፤ 2019 ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት የግዥ አፈጻጸም አዲስ መመሪያ ነው።

በከተማይቱ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ በኩል የወጣው ይህ መመሪያ፤ ላለፉት 17 ዓመታት ገደማ የዋና ከተማዋ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሲከተሉት የቆዩትን የግዥ ስርዓት ተክቷል። አዲሱ መመሪያ የመንግስት ግዥ “በውድድር ላይ የተመሰረተ እና ለወጣው ገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ ማስገኘት የሚያስችል” የማድረግ ዓላማ አለው።

“ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ እና ከሙስና የጸዳ” የመንግስት የግዥ እና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እና “በዘርፉ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር” መቅረፍ ሌሎቹ የመመሪያው ዓላማዎች ናቸው። አዲሱ መመሪያ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት የሚተዳደሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወይም ተቋማት በሚፈጽሙት ግዥ ላይ “በሙሉ ወይም በከፊል” ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

ይሁንና መመሪያው የከተማው የልማት ድርጅቶችን እና በማዕከል የሚፈጸሙ የመድኃኒት አቅርቦቶች እና የህክምና መሳሪያ ግዥዎችን አያካትትም። መመሪያውን የመተግበር ግዴታ የተጣለባቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ናቸው።

እነዚህ መስሪያ ቤቶች “ዕቃ፣ የግንባታ ዘርፍ ስራዎች፣ የምክር አገልግሎት ወይም ከምክር ውጪ የሆነ አገልግሎት” ከአቅራቢዎች ሲገዙ፤ ሊከተሏቸው የሚገቧቸው አካሄዶች መመሪያው በዝርዝር አስቀምጧል። “ግልጽ ጨረታ”፣ “ውስን ጨረታ” እና “በቀጥታ የሚፈጸም ግዥን” የሚፈቅደው አዲሱ መመሪያ፤ በእነዚህ ጨረታዎች እና ግዥዎች ለሚሳተፉ “የስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት” የተለያዩ ማበረታቻዎችን ደንግጓል። 

መመሪያው “የስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት” በሚል ከበየናቸው ውስጥ “የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ማህበራት” እንዲሁም  “የህብረት ስራ ማህበራት” ይገኙበታል። በሌሎች ህጎች “የስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት” ተብለው የተለዩ “አካላትም” በብያኔው ውስጥ ተካትተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች እነዚህን ተቋማት እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ግንባታ ማሰራት እንደሚችሉ አዲሱ መመሪያ ፈቃድ ሰጥቷል። መስሪያ ቤቶቹ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ “የግንባታ ግብአቶች፣ የእንጨት እና የብረታ ብረት ውጤቶችን፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶችን” ከእነዚሁ ተቋማት መግዛት እንደሚችሉም በመመሪያው ላይ ተቀምጧል። 

የከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶች የግንባታ ስራም ይሁን የቁሳቁስ ግዢውን ከስራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት ሲያከናውኑ፤ “አግባብነት ያለውን የግዥ ዘዴ በመጠቀም” በጨረታ ማወዳደር ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና መስሪያ ቤቶቹ በዚህ መንገድ በሚፈጽሟቸው ግዥዎች የገንዘብ መጠን ላይ መመሪያው ገደብ አኑሯል። 

በመመሪያው መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለተመሳሳይ ግዥዎች በአንድ በጀት ዓመት የግንባታ ግዢ መፈጸም የሚችሉት እስከ 200 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። መስሪያ ቤቶቹ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶች፣ የእንጨት እና የብረታ ብረት ውጤቶች፣ ምግብ እና የምግብ ነክ ምርቶች ግዥዎችን የሚፈጽሙ ከሆነ፤ የገንዘብ መጠኑ በአንጻሩ ከ20 ሚሊዮን ብር መብለጥ እንደሌለበት በመመሪያው ላይ ተደነግጓል። 

አዲሱ መመሪያ በአዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የግዥ ጨረታዎች፤ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ድርጅቶች ሲደረጉ የነበሩ ውስን ማበረታቻዎችን ያስቀጠለ ነው። ከሐምሌ 2002 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ የቆየው የቀድሞው የግዥ መመሪያ በውስጡ ከያዛቸው መርሆዎች አንዱ፤ “የከተማውን ኢኮኖሚ የሚደግፉ የሀገር ውስጥ አምራቾችን፣ ኩባንያዎችን እና አነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታት” የሚል ነበር።

የቀድሞው መመሪያ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት አዋጅ መሰረት የተቋቋሙ ድርጅቶች፤ “ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር በሚያደርጉት ውድድር ሶስት ከመቶ ልዩ አስተያየት” እንደሚደረግላቸው የሚገልጽ ድንጋጌ ነበረው። አነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት በሚሳተፉባቸው የመንግስት የግዥ ውድድሮች “የህጋዊነት ማስረጃ በማሳየት” የጨረታ ሰነድ ያለ ክፍያ በነጻ እንዲሰጣቸው ይኸው መመሪያ ችሮታ ሰጥቷቸዋል።

እነዚህ ማበረታቻዎች በአዲሱ መመሪያ ውስጥ ተካትተው እንዲቀጥሉ ተደርገዋል። በዚህም መሰረት ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት ያመረቷቸውን ዕቃዎች ለመንግስት መስሪያ ቤቶች ለመሸጥ “በሚሳተፉበት ማንኛውም ጨረታ” “ልዩ አስተያየት” ይደረግላቸዋል። ማህበራቱ ልዩ አስተያየት የሚደረግላቸው፤ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚያቀርቡት “የራሳቸው የሆኑ የስራ ውጤት ምርቶችን ለማቅረብ ብቻ” እንደሆነ በመመሪያው ላይ ተቀምጧል። 

ማህበራቱ ከሌሎች የውጭ አገር እና የሀገር ውስጥ ተጫራቾች ጋር በሚሳተፉበት ማንኛውም ጨረታ፤ “ሶስት ከመቶ ልዩ አስተያየት” እንደሚሰጣቸው መመሪያው ደንግጓል። ይህ የልዩ አስተያየት ነጥብ፤ መስሪያ ቤቶቹ “የቴክኒክ ሃሳብ በሚገመግሙበት እና በሚያወዳድሩበት ወቅት” የሚሰጥ ነው።

ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራቱ “ልዩ አስተያየት” ተደርጎላቸው ከሌሎች ተጫራቾች ጋር እኩል ነጥብ ቢያመጡ “ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው” መመሪያው ያትታል። እነዚህን ማበረታቻዎች ለማግኘት ግን በማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ አነስተኛ እና ጥቃቅን ማህበራት “አግባብነት ባለው የአነስተኛ እና ጥቃቅን የስራ ዕድል ፈጠራ ህግ መሰረት የተቋቋሙ” መሆን አለባቸው። 

ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራቱ በሚሳተፉባቸው ጨረታዎች ውስጥ ከተፎካካሪዎቻቸው “ልዩ አስተያየት” የሚደረግላቸው እስከ አስር ሚሊዮን ብር በሚያወጡ ግዢዎች ብቻ እንደሆነ በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። የመንግስት ድርጅቶች የሚፈጽሙት ግዢ ከዚህ የገንዘብ መጠን ከበለጠ፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራቱ እንዲወዳደሩ ቢፈቀድላቸውም “ልዩ አስተያየት” ግን አይደረግላቸውም። 

ጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራቱ በጨረታ ሲሳተፉ ካደራጃቸው ተቋም “የመልካም ስራ አፈጻጸም ማስረጃ” ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። “ፈቃዳቸውን ለሌላ ሶስተኛ ወገን ያላስተላለፉ” እንዲሁም “በጥቃቅን ወይም በአነስተኛ ብቻ ተደራጅተው የቆዩ መሆኑን” የሚገልጽ ደብዳቤ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው በመመሪያው ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

We are hiring!