በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ከበደ አሰፋ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓርቲው አስታወቀ። በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብር ጉዳዮች ችሎት ፊት የቀረቡት አቶ ከበደ፤ ለነገ በስቲያ ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ፓርቲው ገልጿል።
ፓርቲው ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 12፤ 2019 ባወጣው መግለጫ፤ ሊቀመንበሩ የታሰሩት “የመንግስት ተወካዮች ነን” በሚሉ አካላት እንደሆነ ጠቅሷል። የአቶ ከበደ እስር “በግለሰብ ፍላጎት” የተፈጸመ መሆኑን የገለጸው ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ፤ ለእርምጃው መንስኤ የሆነው ፓርቲው ከሁለት ቀናት በፊት ያወጣውን መግለጫ መሆኑን አመልክቷል።
ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ባለፈው ረቡዕ ያወጣው መግለጫ የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ነበር። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር በክልሉ “የተገኘውን ለውጥ አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አካሄዶች እየታዩበት ነው” ሲል ተችቷል።

ፓርቲው ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው፤ የባለአደራ አስተዳደሩ በቅርቡ የሰጣቸውን ሹመቶች ነው። በሁሉም የትግራይ ክልል ዞኖች፣ የክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች፣ በዋነኝነት ደግሞ በመቐለ ከተማ እና በትግራይ ደቡብ ምስራቅ ዞን የተሰጡት ሹመቶች “ለአንድ የፖለቲካ ኃይል የወገነ ነው” ሲል ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ በረቡዕ መግለጫው ነቅፏል።
የፌደራል መንግስት ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ለትግራይ ክልል ያቋቋመው የባለአደራ አስተዳደር የሚያዘጋጃቸው ሁሉም መድረኮች፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ያገለለ መሆኑንም ፓርቲው በተጨማሪነት አንስቶ ነበር። ይህ አካሄድ በሹመት አሰጣጥ ላይ የተፈጸመው “ስህተት”፤ ሆን ተብሎ የተደረገ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነም ፓርቲው በመግለጫው አክሏል።
ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ በረቡዕ መግለጫው፤ በአሁኑ ወቅት በአመራር ደረጃ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ላይም ትችት ሰንዝሮ ነበር። ግለሰቦቹ “በጸረ ህዝብ ተግባራት ተሰማርተው የነበሩ” እና “ህዝባዊ ስርዓት ተቋቁሞ ሊጠየቁ የሚገባቸው” እንደነበሩ በመግለጫው የወነጀለው ፓርቲው፤ በአሁኑ ወቅት የነበሩበትን ፓርቲ እና አደረጃጀት ቀይረው “የብልጽግና ፓርቲ አባላት” መሆናቸውን ገልጿል።

በስም ያልተቀጠሱት ግለሰቦች፤ የገዢው ፓርቲ አባላት መሆናቸውን “ላለፈው ወንጀላቸው መደበቂያ” እና “ከተጠያቂነት ማምለጫ አድርገው” የሚቆጥሩ እንደሆኑም ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ በመግለጫው ከስሶ ነበር። ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫም፤ በክልሉ “መንግስት ነን” የሚሉ አካላት “አግባብ ባልሆነ መንገድ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን የሚያንገላቱ” መሆኑን ጠቅሷል።
የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ሊቀመንበር አቶ ከበደ እስርም የእዚሁ ማሳያ መሆኑን ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል። “አቶ ከበደ አሰፋ ህወሓት ከስሩ እንዲጠፋ፣ ለሁሉ የምትሆን እንዲሁም ሁሉም አይነት ሃሳብ የምታስተናግድ ትግራይ እንድትፈጠር የታገሉ ሰላማዊ ታጋይ ናቸው” ያለው ፓርቲው፤ “በሰላማዊ ትግል ሀሳብ አምኖ የሚታገል ድርጅትንም ይሁን ግለሰብ ማፈን ስርዓትን የሚያዋርድ ተግባር መሆኑን” አስገንዝቧል።
“ፓርቲያችን ሲመሰረት የህዝባችን ድምጽ ሆኖ እንዲታገል እንጂ ግልጽ ችግሮችን እያየ በስጋት እንዲያልፍ አይደለም” ያለው ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ፤ ይህ የአቶ ከበደ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የፓርቲው አመራር እና አባላት “ጽኑ አቋም” መሆኑን አስታውቋል። ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ በጳጉሜ 2015 ዓ.ም. የምስረታ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት፤ ፓርቲው የተቋቋመው በትግራይ ክልል “ተንሰራፍቷል” ያለውን “ጭቆና እና የአንድ ፓርቲ ስርዓት” ለመታገል እንደሆነ ገልጾ ነበር።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በታህሳስ 2016 ዓ.ም. ያገኘውን ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ፤ ከምስረታው ጀምሮ በሊቀመንበርነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ከበደ አሰፋ ናቸው። አቶ ከበደን ካለፈው ሐሙስ ህዳር 10፤ 2019 ጀምሮ በቁጥጥር ስር ያዋሉት የፌደራል መንግስት የህግ አካላት፤ “ፈጣን ምርመራ” በማድረግ “ፍትህ የግለሰቦች እንዳልሆነች” እንዲያረጋግጡ ፓርቲው በዛሬው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































