የመቐለ አምስት ክፍለ ከተሞች አመራሮች ምርጫ ዛሬ ተካሄደ 

በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ የሚገኙ አምስት ክፍለ ከተሞችን ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሚያስተዳድሩ አመራሮች በዛሬው ዕለት ተመረጡ። ከክፍለ ከተሞቹ አንዱ በሆነው ዓዲ ሓቂ፤ በምርጫው ለመሳተፍ ከተገኙ ነዋሪዎች መካከል ሰባት ሰዎች በስም ተጠርተው እንዲወጡ መደረጋቸው ተቃውሞ አስነስቷል።

የዛሬው የክፍለ ከተሞች ምርጫ፤ የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል ያቋቋመው የባለአደራ አስተዳደር ስራ ከጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ ነው። ከግማሽ ሚልዮን በላይ ህዝብ ይኖርባታል ተብሎ የሚገመትባት የመቐለ ከተማ ሰባት ክፍለ ከተሞች አሏት።

በርካታ የንግድ ማዕከላት እና ጥንታዊው የከተማዋ ክፍል ያለበት “ቀዳማይ ወያነ” የተባለው ክፍለ ከተማ እና የክልሉ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲሁም በርካታ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙበት “አይደር” ክፍለ ከተማን የሚያስተዳድሩ አመራሮች የተመረጡት ባለፈው ጥቅምት 3፤ 2019 ነበር። ይህ ምርጫ የተካሄደው የባለአደራ አስተዳደሩ ከመቋቋሙ አስቀድሞ ነው።  

ዛሬ እሁድ ጥቅምት 15 አመራሮቻቸውን የመረጡ ክፍለ ከተሞች ዓዲ ሓቂ፣ ኩሓ፣ ሓወልቲ፣ ሰሜን እና ሓድነት ናቸው። ለምርጫው በየክፍለ ከተሞቹ የተዘጋጁ አዳራሾች፤ በመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ተሞልተው ታይተዋል። ወደ አዳራሾቹ ለመግባት ከሚደረገው ፍተሻ ጀምሮ የአካባቢዎቹን ጸጥታ ሲያስጠብቁ የነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደነበሩ የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ምርጫን ለመታዘብ በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢም ተመሳሳዩ የጸጥታ አከባበር ሁኔታን አስተውሏል። በኖርዘርን ስታር ሆቴል አዳራሽ በተካሄደው በዛሬው የክፍለ ከተማ አመራሮች ምርጫ ለመሳተፍ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በስፍራው መሰባሰብ የጀመሩት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነበር።

የምርጫው ሂደት የተመራው “ከፌደራል መንግስት መላካቸውን” በገለጹ ሶስት ግለሰቦች አማካኝነት ነበር። እነዚሁ ግለሰቦች ከተሰብሳቢዎቹ መካከል የሰባት ሰዎችን ስም በመጥራት፤ ከስብሰባ አዳራሹ እንዲወጡ ትዕዛዝ ሲሰጡ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ታዝቧል።

ሆኖም ይህ ትዕዛዝ በምርጫው ለመሳተፍ በተገኙ የተወሰኑ ወጣቶች ዘንድ ተቃውሞ አስከትሏል። ወጣቶቹ ከአዳራሽ በፌደራል ፖሊስ ታጅበው እንዲወጡ የተደረጉት ግለሰቦች እንዲመለሱ ቢጠይቁም፤ ከአስተባባሪዎቹ ጋር ሳይስማሙ ቀርተዋል።

ይህን ተከትሎም እነዚሁ ወጣቶች የምርጫ ሂደቱን ረግጠው በመውጣት፤ እርምጃውን መቃወማቸውን አሳይተዋል። በሃድነት ክፍለ ከተማ ምርጫ ላይም፤ የተወሰኑ ሰዎች ወደ አዳራሽ እንዳይገቡ መደረጋቸው ቅሬታ መፍጠሩ ተዘግቧል።

በዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ በነበረው የምርጫ ሂደት፤ ዘጠኝ ግለሰቦች ተጠቁመው አምስት ሰዎች ተመርጠዋል። ለአመራርነት ከተጠቆሙት ግለሰቦች አንዱ፤ በፖሊስ ከአዳራሽ እንዲወጡ ከተደረጉት ሰባት ሰዎች መካከል በመሆኑ በቂ ድምጽ ሳያገኝ ቀርቷል።

የዛሬው ምርጫ የተከናወነው እጃቸውን በድጋፍ ያወጡ ተሰብሳቢዎችን በመቁጠር እንደነበር የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። በዚህ መልኩ የተመረጠው የክፍለ ከተማው አስተዳደር፤ በትግራይ ክልል መደበኛ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የባለአደራ አስተዳደር አካል ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቁሟል።

በትግራይ ክልል ከጦርነት በፊት በነበረው አሰራር፤ የእነዚህ ክፍለ ከተሞች ተጠሪነት ለመቐለ ከተማ አስተዳደር ነበር። አስተዳደሩ በወቅቱ ሲመራ የቆየው፤ በከተማይቱ ምክር ቤት በሚመረጥ ከንቲባ ነው።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ፤ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ምርጫ ከምክር ቤት ወደ ጊዜያዊ አስተዳደር ሹመት ተቀይሯል። በዶ/ር ሙሉ ነጋ ይመራ የነበረው የወቅቱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የመቐለ ከተማን በጊዜያዊ ከንቲባነት እንዲመሩ አቶ አታክልቲ ኃይለሥላሴ ሾሞ ነበር።

ህወሓት መቐለ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ የከተማይቱ ምክር ቤት አቶ ይትባረክ አምሃን በከንቲባነት ሾሟል። አቶ ይትባረክ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ወቅትም የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው ቀጥለዋል። 

ጊዜያዊ አስተዳደሩን በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ከህወሓት አመራሮች ጋር ከተቃቀሩ በኋላ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስን ከንቲባ አድርገው ሾመዋል። ይህን ሹመት ያልተቀበለው ህወሓት ዶ/ር ረዳኢ በርሀን በከንቲባነት በመሾም የመቐለ ኤፍ ኤም የሬድዮ ጣቢያን እንዲቆጣጠሩ አድርጓል። 

በዚህ ውዝግብ ምክንያት የመቐለ ከተማ አስተዳደር ለተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ ቆይቷል። አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳትነታቸውን ለሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ካስረከቡ በኋላ የመቐለ ከተማ ምክር ቤት አቶ ሃይላይ አረጋዊን በሰኔ 2018 ዓ.ም. ከንቲባ አድርጎ ሾሟል። 

አቶ ሃይላይ ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ በትግራይ እና አዋሳኝ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ውጊያ ተከትሎ የህወሓት ባለስልጣናት የመቐለ ከተማን ለቅቀው እስኪወጡ ድረስ በዚሁ ኃላፊነታቸው ላይ ቆይተዋል። ለቀናት ያለ አመራር የቆየችው የመቐለ ከተማ፤ አዲስ ከንቲባ የተሾመላት ከሳምንት በፊት ነበር። 

የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙን ይፋ ባደረገበት ጥቅምት 6፤ 2019፤ ዶ/ር ሺሻይ አማረ የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው መሾማቸውን አስታውቋል። ዶ/ር ሺሻይ ከዚህ ሹመታቸው አስቀድሞ በኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የተቋማት ቁጥጥር፣ ኢንስፔክሽን እና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ለሁለት ዓመት ያህል ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)