የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙሃንን “ማን አህሎኝነትን እና አይነኬነትን” እንደማያስተናግድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ። መገናኛ ብዙሃን “ስንት ገንዘብ ይዣለሁ? ስንት አመት ኖሬያለሁ?” በሚል “ከህግ በላይ” ሆነው መኖር እንደማይችሉም የቦርድ ሰብሳቢው አስጠንቅቀዋል።
አቶ ሬድዋን ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጡት፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን “ሪፖርተር” እና “ዘ ሪፖርተር” የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ ጋዜጦች “ላልተወሰነ ጊዜ” ከህትመት እና ከስርጭት “ሙሉ በሙሉ” መታገዳቸውን ካስታወቀ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው። ባለስልጣኑ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ የጋዜጣው የበይነ መረብ ማሰራጫ ላይም ተመሳሳይ የእገዳ ውሳኔ መተላለፉንም አስታውቆ ነበር።
ይህ የእገዳ ውሳኔ በማህበራዊ የትስስር መድረኮች ከፍተኛ ትችቶች ያስተናገደ ሲሆን ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሞታል። እርምጃው የኢትዮጵያ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ላይ “እየፈጸመ ያለው ጥቃት አካል ነው” ያለው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ እገዳው እንዲነሳ በይፋ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን ስራዎች የመቆጣጠር እና የመገምገም ስልጣኖች በአዋጁ የተሰጡትን ቦርድ በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ሬድዋን፤ ለእነዚህ ትችቶች ምላሽ የሰጠ የሚመስል ንግግር ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 26፤ 2019 አድርገዋል። አቶ ሬድዋን ንግግሩን ያደረጉት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያስገነባውን የኢትዮጵያ ሚዲያ የልህቀት ማዕከል በመረቁበት ወቅት ነው።
በመርሀ ግብሩ ላይ 16 ደቂቃ ገደማ የወሰደ ንግግር ያደረጉት አቶ ሬድዋን፤ የመጀመሪያውን አጋማሽ የተጠቀሙት “በመናገር ነጻነት እና ተጠያቂነት” ላይ ያተኮሩ ንድፈ ሃሳባዊ ጉዳዮችን ለማብራራት ነው። የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ዳይሬክተር ጄነራሉ ይህንን የንግግር ክፍላቸውን ያቀረቡት አስቀድመው ያዘጋጁትን ጹሁፍ በማንበብ ነበር።
ለሰሞነኛ ጉዳዮች ምላሽ የሰጠ የመሰለው የአቶ ሬድዋን ቀጣይ የንግግር ክፍል፤ የሚዲያ ነጻነት፣ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ላይ ያተኮረ ነው። አቶ ሬድዋን በንግግራቸው “የለውጥ” ባሏቸው ያለፉት ስምንት ዓመታት፤ በግል የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን በሬድዮም ሆነ በቴሌቪዥን “እየሰፋ መሄዱን” አንስተዋል።
በኢትዮጵያ “የህትመት ሚዲያ እየቀነሰ መሄዱን” በንግግራቸው ያመኑት የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ቦርድ ሰብሳቢ፤ “እየቀነሰ የሄደው በኢትዮጵያ ውስጥ [ብቻ] ሳይሆን በዓለም ነው” ሲሉ ሂደቱ ዓለም አቀፍ ገጽታ ያለው መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ለዚህ አንዱ መፍትሔው “ቴክኖሎጂውን ተከትሎ፣ የሀገር እድገትን ተከትሎ፣ አለምን ተከትሎ ራስን ማዘመን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ እገዳን ተከትሎ በማህበራዊ የትስስር ገጾች ከቀረቡ ሃሳቦች መካከል የተወሰኑት፤ በኢትዮጵያ በብቸኝነት ቀርቶ የነበረው የግል አማርኛ ጋዜጣ በባለስልጣኑ ውሳኔ ከህትመት ውጭ መደረጉን ተችተው ነበር። “ሪፖርተር” ጋዜጣ ከጳጉሜ 6፤ 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 31 ዓመታት በህትመት ላይ የቆየ መገናኛ ብዙሃን ነው።
አቶ ሬድዋን በዛሬው ንግግራቸው “ረጅም ዓመት ቆይቻለሁ” በሚል የሚንጸባረቅ “ማን አህሎኝነትን እና አይነኬነትን” የኢትዮጵያ መንግስት እንደማያስተናግድ ጠንከር ባሉ ቃላት አስታውቀዋል። “የማይጠየቅ ብዙሃን መገናኛ አይኖርም” ያሉት አቶ ሬድዋን፤ “መንግስትም ይገሰጻል ሚዲያም በኃላፊነት ይጠየቃል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“የማይነካ መንግስት የለም። የማይተች መንግስት የለም፣ ፓርላማ ተቹ፣ ዳኛ ተቹ፣ ፍርድ ቤት ተቹ፣ አስፈጻሚውን ተቹ። ነገር ግን የጋራ ሀገር አለ። ‘ስንት ኤምባሲ ያውቀኛል? ስንት ፈረንጅ ይናገርልኛል? ስንት ገንዘብ ይዣለሁ? ስንት ዓመት ኖሬያለሁ?’ በሚል ህጉን እስከ ጥግ ተጠቅሞ ከህጉ በላይ መኖር ግን አይቻልም”
“የማይነካ መንግስት የለም። የማይተች መንግስት የለም፣ ፓርላማ ተቹ፣ ዳኛ ተቹ፣ ፍርድ ቤት ተቹ፣ አስፈጻሚውን ተቹ። ነገር ግን የጋራ ሀገር አለ። ‘ስንት ኤምባሲ ያውቀኛል? ስንት ፈረንጅ ይናገርልኛል? ስንት ገንዘብ ይዣለሁ? ስንት ዓመት ኖሬያለሁ?’ በሚል ህጉን እስከ ጥግ ተጠቅሞ ከህጉ በላይ መኖር ግን አይቻልም” ሲሉ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ዳይሬክተር ጄነራሉ አስጠንቅቀዋል።
አቶ ሬድዋን መገናኛ ብዙሃንን ከውጭ ሀገር ኤምባሲዎች ጋር በማያያዝ ትችት ሲያቀርቡ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር አጋማሽ በተካሄደው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የልህቀት ማዕከል ስልጠና ማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ፤ በስም ያልጠቀሷቸው መገናኛ ብዙሃን በውጭ ሀገራት እንደሚደገፉ እንደሚያውቁ ተናግረው ነበር።
“እንዳንድ ሚዲያዎችን ስናስጠነቅቅ፤ የማን ሀገር መግለጫ ቀድሞ እንደሚወጣ እናውቃለን…የሆነ ሚዲያ ላይ የሆነ ነገር ስትሉ፣ ቀድሞ የሚሄደው ኤምባሲ ከፋይ ነው ማለት ነው” ሲሉ አቶ ሬድዋን በዚሁ ማብራሪያቸው ወንጅለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን ለሶስት ዓመታት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን የሰሩት አቶ ሬድዋን በዛሬው ንግግራቸው፤ መገናኛ ብዙሃን “ከኢትዮጵያ እና ከመንግስቷ በላይ አቅም እንዳላቸው ሊሰማቸው እንደማይገባ” ማስጠንቀቂያ አዘል ጥቆማ ሰጥተዋል።
“ከአእምሯችን ማውጣት ያለብን፤ ሚዲያ የሚባል ላይሰንስ የደፋን ጊዜ፤ ከሀገሪቱ ፓርላማም፣ ከሀገሪቱ ዳኛም፣ ከሀገሪቱ መንግስትም በላይ እንደሆንን እንዳይሰማን ማድረግ ነው። ድርሻ አለን፣ ኃላፊነት አለብን። መንግስት ይጠየቃል፣ ሚኒስትሮች ይጠየቃሉ፣ ዳኛ ይጠየቃል፣ ፓርላማ ይተቻል፣ ሚዲያም ይተቻል። ይተቻል ብቻ ሳይሆን፤ ሁሉም ሰው እንደሚጠየቀው ሚዲያም ይጠየቃል” ብለዋል አቶ ሬድዋን።
አቶ ሬድዋን በኢትዮጵያ ዘመቻ በማካሄድ የሚቀየር ነገር እንደሌለም በዛሬው ንግግራቸው በአጽንኦት አሳስበዋል። የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢው ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በ“ሪፖርተር” ጋዜጣ ላይ የወሰደውን እገዳ መልሶ እንዲያጤነው እና እርምጃውን እንዲቀለብስ በርካቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
“በዘመቻ የሚሆን አይኖርም። አርባ ጊዜ ተመክረህ፣ አርባውም ጊዜ አውቀህ ካጠፋህ በኋላ አንድ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥህ፤ ዙሪያው ላይ ዘመቻ በማድረግ የሚመጣ ከሆነ፤ ‘ከኢትዮጵያ በላይ አቅም አለኝ አለኝ’ ብሎ ማሰብ ይሆናል ማለት ነው። [ስለዚህ] ባለቤቷ ኢትዮጵያ አትሆንም ማለት ነው። ‘ባለቤቱን የተማመነ ምንድነው’ የሚባለው አይነት ይሆናል። እሱ አይሰራም። በተለይ እዚህ ሀገር አይሰራም” ሲሉ አቶ ሬድዋን በዛሬው ንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ለመገናኛ ብዙሃን የሚሰራው “የኢትዮጵያ ህግ ምን ይላል? የኢትዮጵያ ፍላጎቷስ ምንድነው፣ የእኔ ድርሻስ ምን ይሆናል?” የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት፤ ጥፋት ተፈጽሞ ሲገኝ ደግሞ “አስቀድሞ ይቅርታ መጠየቅ እንደሆነ” አቶ ሬድዋን አሳስበዋል። “እንደዚያ ያደረጉ ሚዲያዎች አሉ። ያላጠፉ ሳይሆን፣ ተሳስተው፣ ተነግሯቸው፣ ታርመው፣ ከዚያ አስተካክለው የሚሰሩ አሉ” ሲሉም የባለስልጣኑ የቦርድ ሰብሳቢ አክለዋል።
“አምስቴም ቢያጠፉ፣ አምስቴም ይታረማል። ዋናው የሚታየው፤ አንድ- ለመታረም ዝግጁ ነው ወይ? [ሁለት] – ያጠፋው ሆን ብሎ በእቅድ፣ እንደ ርዕሰ አንቀጽ አስቦት ነው ወይ የሰራው ወይስ ጋዜጠኛ ነው ያበላሸበት? የሚለው ነው። ባለቤት የሚያጠፋው፣ አመራር የሚያጠፋው፣ ጋዜጠኛ የሚያጠፋው ተቆጥሮ፣ ስንት ጊዜ ነው ተብሎ፣ መነሻው ምንድነው ተብሎ እርግጠኛ ካልተሆነ፤ የሚሳቀል ጋዜጠኛ አይኖርም። የሚቀጭጭ ሚዲያም አይኖርም” ብለዋል አቶ ሬድዋን።
“አንድ ሚዲያ በመንቀል ሃሳብ ማዳፈን አይቻልም። አንድም ሚዲያ ቢሆን ግን ስርዓት አልበኛ ሲሆን፣ ከህግ በላይ ሲሆን፣ መታረም ካልቻለ፤ አይነኬነት ባህል ይሆናል” ሲሉም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ተደምጠዋል። “አሁን ሁለት ጋዜጠኛ፣ ሶስት ጋዜጠኛ በማንገላታት፣ አንድ ሚዲያ፣ ሁለት ሚዲያ በማገድ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ማስፋት አይደለም ዓላማው። መማሪያ ማድረግ ነው” ሲሉም አክለዋል።
እርሳቸው ይበሉ እንጂ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን የሚሰጣቸው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች፣ የሚያስተላልፋቸው እገዳዎች እና የውጭ ጋዜጠኞችን ከኢትዮጵያ የማባረር እርምጃዎች፤ በሀገሪቱ “ተቺ ዘገባን ለማጥፋት ሆን ተብሎ እየተደረገ ያለ ዘመቻ አካል ነው” የሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































