የትግራይ ቴሌቪዥን ይዘቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

የትግራይ ቴሌቪዥን የሚያስተላልፋቸውን ይዘቶች “በሚያሰራጩ እና በሚያስተጋቡ” መገናኛ ብዙሃን ላይ “አስፈላጊውን ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እና እርምጃዎች” እንደሚወስድ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስጠነቀቀ። ባለስልጣኑ ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው፤ በትግራይ ክልል መንግስት ስር የሚተዳደረውን ቴሌቪዥን ጣቢያ ከዛሬ ሰኞ መስከረም 11፤ 2019 ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” ካገደ በኋላ ነው።

መስሪያ ቤቱ እርምጃውን የወሰደው፤ በኢትዮጵያ “አካታች የሽግግር መንግስት” ለመመስረት ያለመ የሰባት አማጽያን ኃይሎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ትብብር መመስረቱ ይፋ የተደረገበት መግለጫ፤ በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ በማግስቱ ነው። ይህ መግለጫ ተቀማጭነታቸውን በትግራይ ክልል ባደረጉ ሌሎች ዜና ማሰራጫዎችም በተመሳሳይ ጊዜ ተላልፏል። 

በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እገዳውን የጣለው ባለስልጣኑ፤ መገናኛ ብዙሃን ተግባራቶቻቸውን በህግ መሰረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ “ክትትል እና ቁጥጥር” የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ተቋም ነው። መስሪያ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤   የትግራይ ቴሌቪዥን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የሀገርን እና የህዝብን ደህንነት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ” መልዕክቶች እየተላለፉበት ነው ሲል ወንጅሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በቴሌቪዥን ጣቢያው “ወደ ግጭት የሚገፋፉ” እና “ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ” መልእክቶች በተከታታይ እየተላለፉበት እንደሚገኙም መስሪያ ቤቱ ባደረገው “የሚዲያ ይዘት ክትትል ግምግማ ማረጋገጡንም” ተቋሙ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። በዚህ ምክንያት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ “ላልተወሰነ ጊዜ” እገዳ መጣሉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እገዳ ሲጥል የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። በሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ፤ የትግራይ ቴሌቪዥን እና ድምጺ ወያነ (DW TV) ከሳተላይት ስርጭት እንዲወርዱ ተደርገው ነበር።

በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ “ተጥሎ የነበረው እገዳ” የተነሳው፤ በኢፌዴሪ መንግስት እና በሕወሓት መካከል በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ እንደነበር የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣኑ በዛሬው መግለጫው አስታውሷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እገዳውን ያነሳው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ባደረገው ውይይት እና “በተደረሰበት ስምምነት መሰረት” እንደነበርም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

ባለስልጣኑ እገዳውን ከማንሳት በተጨማሪ መገናኛ ብዙሃኑ “ወደ ሕገ መንግስታዊ እና ሙያዊ መስመር እንዲመለስ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ” መየቱንም በመግለጫው አመልክቷል። መስሪያ ቤቱ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው፤ ለትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች እና ባለሙያዎች የሰጠውን “የሰላም ግንባታ” እና “የሙያ ብቃት ማሳደጊያ” ስልጠናዎችን ነው።

የትግራይ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሰጠውን “ዕድል ተጠቅሞ” እና “የሙያ ስነ ምግባር አክብሮ” አገልግሎት መስጠት ይገባው እንደነበርም በመግለጫው ላይ አስገንዝቧል። ይህን ባለማድረጉ እገዳ እንደተጣለበት የተገለጸውን የትግራይ ቴሌቪዥን፤ “እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀም” “በጥብቅ የተከለከለ” መሆኑን ባለስልጣኑ በዛሬው መግለጫው አስጠንቅቋል። 

መስሪያ ቤቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው ለዲጂታል፣ ለብሮድካስት እና ለህትመት መገናኛ ብዙሃን ነው። እነዚህ መገናኛ ብዙሃን የትግራይ ቴሌቪዥን “በህገ ወጥ መንገድ” የሚያስተላልፋቸውን “ይዘቶች” “እንዳያሰራጩ እና እንዳያስተጋቡም” ክልከላ ተጥሎባቸዋል።

ይህንን የባለስልጣኑን ክልከላ ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም መገናኛ ብዙሃን መስሪያ ቤቱ “አስፈላጊውን ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች” የሚወስድ መሆኑንም አጥብቆ አሳስቧል። በ2013 ዓ.ም. የወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የሚወስደው “በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን አሊያም አዋጁን ተከትለው የሚወጡ ደንብ ወይም መመሪያዎችን በተላለፉ መገናኛ ብዙሃን ላይ” እንደሆነ ይደነግጋል።

በአዋጁ በአስተዳደራዊ እርምጃነት ከተዘረዘሩት ውስጥ “ጥሰት የፈጸመውን የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድን ፈቃድ ማገድ ወይም መሰረዝ” የሚለው ይገኝበታል። ባለስልጣኑ ባለፈው ዓመት ጥር እና የካቲት ወር በተከታታይ በወሰዳቸው እርምጃዎች የ“ዋዜማ” እና የ“አዲስ ስታንዳርድ” መገናኛ ብዙሃን የምዝገባ የምስክር ወረቀት መሰረዙ ይታወሳል። 

ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ በአዋጁ ከተሰጡት አስተዳደራዊ እርምጃዎች አንዱ የሆነውን “የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ”፤ ለአርትስ ቴሌቪዥን እና ለአሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ባለፈው ሰኔ ወር “ለመጨረሻ” ጊዜ መስጠቱ አይዘነጋም። ባለስልጣኑ ባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ ባወጣው መግለጫ፤ የጄ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ ስርጭት የሚያስተላልፍበትን የአየር ሞገድ ለስድስት ወራት እንዳይጠቀም  መታገዱንም አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)