በአልማክቱም ፋውንዴሽን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ በማስጠንቀቂያ ተነሳ

በሃሚድ አወል

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በአልማክቱም ፋውንዴሽን ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ በመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ማንሳቱን አስታወቀ። ኤጀንሲው እገዳውን ያነሳው ድርጅቱ የፈጸመውን የህግ ጥሰት አምኖ በመቀበሉ እና ለስህተቱም ይቅርታ በመጠየቁ መሆኑን ገልጿል።

አል-ማክቱም ፋውንዴሽን ለሶስት ወራት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በኤጀንሲው እገዳ የተጣለበት በሐምሌ 2013 ነበር። ከፋውንዴሽኑ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ሁለት ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች እገዳ ተጥሎባቸዋል። ሁለቱ የተራድዖ ድርጅቶች የሆላንዱ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ናቸው። 

አል-ማክቱም ፋውንዴሽንን ለእገዳ ካደረጉት ሁለት ምክንያቶች የመጀመሪያው፤ “የውጭ ሀገር ዜጎችን ያለስራ ፍቃድ አሰማርቷል” የሚል ነው። ድርጅቱ በዚህ ረገድ የፈጸመው የህግ ጥሰት ላይ ተገቢውን እርምት ያደረገ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ያለስራ ፍቃድ ያሰማራቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ከሀገር የወጡበትን መረጃ በማቅረቡ እገዳው እንደተነሳለት ኤጀንሲው አስታውቋል። 

ፋውንዴሽኑ ለመታገዱ በሁለተኛነት የተጠቀሰበት ምክንያት “የሀገሪቱን ህገ መንግስት ባለማክበር እና ለህግ ተገዢ ባለመሆን፤ በማን አለብኝነት እንቅስቃሴ ማድረጉ በመረጋገጡ” መሆኑን ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዘው የህግ ጥሰት፤ ፋውንዴሽኑ በአዲስ አበባ ከገነባቸው ሁለት ትምህርት ቤቶች ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑም ተመልክቷል።  

በዱባይ ምክትል ገዢ ሼክ ሀምዳን ቢን ራሺድ አል-ማክቱም የተመሰረተው ፋውንዴሽኑ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ69 ሀገራት ላይ ትምህርት ላይ መሰረት ያደረገ የእርዳታ ስራዎችን ይሰራል። ፋውንዴሽኑ በ22 የአፍሪካ ሀገራት 40 ትምህርት ቤቶችን ያቋቋመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም በአዲስ አበባ የካ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ትምህርት ቤቶች አስገንብቶ ከሶስት ዓመታት በፊት ስራ አስጀምሯል። 

ድርጅቱ በኢትዮጵያ በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሆነውን የኮቪድ 19 ፕሮቶኮሎች በመጣስ፣ በትምህርት ቤቱ ስም የሚመጣውን በጀት ከተቋቋመበት አላማ ውጭ ለአረብኛ ቋንቋ ማስፋፊያ ማዋል እና የሰራተኞችን ጥያቄ በህገ ወጥ መንገድ ለማፈን ሞክሯል የሚሉ ተጨማሪ ክሶች በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ቀርበውበት ነበር።

የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ትግስት ዳኝነት፤ ፋውንዴሽኑ የቀረቡበትን ክሶች የሚያስረዱ ማስረጃዎችን ማቅረቡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ኤጀንሲው ትላንት ሐሙስ መስከረም 20 ባወጣው መግለጫ፤ ማስረጃዎቹን መመርመሩን ገልጿል። 

“ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የጥፋት ሪከርድ የሌለበት በመሆኑ፣ ስህተቱንም አምኖ በማስተካከሉ እንዲሁም የያዛቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለሃገር ጥቅም ያላቸው በመሆኑ የተሰጠው እገዳ በመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ የተነሳ መሆኑን እንገልጻለን” ሲል ኤጀንሲው በትላንቱ መግለጫው አስታውቋል።      

ከአል-ማክቱም ፋውንዴሽን ጋር እገዳ የተላለፈባቸው የሆላንዱ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስልን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር፤ “እስካሁን ማስረጃ አላቀረቡም፣ እኛም እያጣራን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ሁለቱ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የታገዱት፤ የሐሰት መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች አሰራጭተዋል በሚል ነው። ድርጅቶቹ ያለኤጀንሲው ፍቃድ እና እውቅና፤ የውጭ ሀገር ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በማሰራት ሌላ ውንጀላ ቀርቦባቸው ነበር።  

የሆላንዱ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በኤጀንሲው ለመታገዱ ተጨማሪ ምክንያትም ተጠቅሶበታል። ድርጅቱ “የሳተላይት ሬዲዮኖችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ አፍራሽ ለሆነ ተግባር እንዲውሉ አድርጓል” በሚል በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ተወንጅሎ ነበር። የኤጀንሲውን እገዳ ተከትሎ፤ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ስራውን ማቋረጡን በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)