የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ የሚያደርግ ሰነድ በናይሮቢ ተፈረመ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ተዋጊዎች አዛዥ ሌፍተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ የሚያደርግ ሰነድ ዛሬ ተፈራረሙ። ሁለቱ አዛዦች የተፈራረሙት ሰነድ፣ በትግራይ፣ በአፋር እና አማራ ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ በአፋጣኝ ማዳረስ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ሁለቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ስምምነቱን የተፈራረሙት፤ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ካለፈው ሰኞ ጥቅምት 28፤ 2015 ጀምሮ ካደረጉት ድርድር በኋላ ነው። ስምምነቱ ሲፈረም በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል የሚደረገውን ድርድር በበላይነት የሚመሩት የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና ከድርድሩ አመቻቾች አንዱ የሆኑት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተገኝተዋል።

ዛሬ በተፈረመው ሰነድ መሰረት፤ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች ለሚገኙ እና እርዳታ ለሚሹ ሁሉ ያለምንም ገደብ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲዳደረስ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። ሁለቱ የጦር አዛዦች ዛሬ በፊርማቸው ባጸደቁት ሰነድ፤ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ሰራተኞች ያለ ምንም እንቅፋት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

ለሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች እና ድርጅቶች የጸጥታ ዋስትና ለመስጠት እንደዚሁም ለሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ለማድረግ የጦር አዛዦቹ መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም አጠቃላይ የትጥቅ መፍታት፣ ታጣቂዎች እንዲበተኑ ማድረግ እና መልሶ ማዋሃድ ፕሮግራም አፈጻጸምን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከዛሬው ፊርማ ስምምነት በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ ሁለቱ የጦር አዛዦች በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በተቀመጠው “የጊዜ ገደብ ትጥቅ የሚፈታበትን እና የመከላከያ ሰራዊት ወደ መቀሌ የሚገባበት ዕቅድ” ላይ መስማማታቸውን ይፋ አድርጓል። የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ በዚሁ መግለጫው፤ ይህ ዕቅድ “በቀጣይ ተግባራዊ ይደረጋል” ቢልም ስለ ጊዜ ገደቡ ግን ዝርዝር ማብራሪያ ሳያቀርብ ቀርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)