በሃሚድ አወል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ወቅታዊ ሀገራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ነገ ማክሰኞ ህዳር 6፤ 2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ ሊሰጡ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ መንግስታቸው ከህወሓት ጋር ያደረገውን ስምምነት በተመለከተ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሶስት የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በነገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር የተመለከቱ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡም የፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ የሁለቱ ምክር ቤቶችን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
ለፓርላማ አመራሮች ቅርበት ያላቸው አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው “የተለየ ጥያቄ ካላችሁ አቅርቡ ተብለን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አቅርበናል” ብለዋል። ይህ መልዕክት “በፓርቲ ተወካይ” እንደተላለፍላቸውም አክለዋል።
ሶስቱም የምክር ቤት አባላት የፌደራል መንግስት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ያደረገው ስምምነት፤ የነገው የፓርላማ ውሎ ዋና አጀንዳ እንደሚሆን ተናግረዋል። አንደኛው የምክር ቤት አባል እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የፓርላማ አባላት ስምምነቱ ላይ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንዳሏቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ አማጽያን ለሁለት ዓመታት ሲያደርጉት የቆዩትን ጦርነት የሚያስቆመውን ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙት፤ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ጥቅምት 23፤ 2015 ነበር። ከፕሪቶሪያው የፊርማ ስነ ስርዓት ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአርባ ምንጭ ከተማ ባደረጉት ንግግር፤ በደቡብ አፍሪካው ድርድር ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሀሳብ “መቶ በመቶ ተቀባይነት አግኝቷል” ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ “ታላቅ ዕድል ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ከእርሳቸው ንግግር አንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ በኬንያ ናይሮቢ የተገናኙት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ኃይሎች ጦር አዛዦች የግጭት ማቆም ስምምነቱ በሚፈጸምበት አካሄድ ላይ ለአምስት ቀናት ሲነጋገሩ ቆይተዋል።
ይህ ንግግር ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ህዳር 3፤ 2015 ሲጠናቀቅ፤ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ሌፍተናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ ስምምነቱን ተግባራዊ የሚያደርግ ሰነድ ተፈራርመዋል። በናይሮቢው የስምምነት ሰነድ መሰረት፤ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች ለሚገኙ እና እርዳታ ለሚሹ ሁሉ ያለምንም ገደብ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲዳረስ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ።
ከዚህ በተጨማሪ፤ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ሰራተኞች ያለ ምንም እንቅፋት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ለሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች እና ድርጅቶች የጸጥታ ዋስትና ለመስጠት እንደዚሁም ለሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ለማድረግ የጦር አዛዦቹ መስማማታቸው በሰነዱ ይፋ ተደርጓል። የጦር አዛዦቹ፤ አጠቃላይ የትጥቅ መፍታት፣ ታጣቂዎች እንዲበተኑ ማድረግ እና መልሶ ማዋሃድ ፕሮግራም አፈጻጸምን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም መስማማታቸውም በሰነዱ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)