በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ ጊዜ እየተፈጠሩ ያሉ አጀንዳዎች እና ነውጦች፤ መንግስት “በሌብነት ላይ የጀመረውን” ዘመቻ እንዲያቆም የሚደረጉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ። መንግስት ሙስናን ለመታገል የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያስታወቁት በወላይታ ሶዶ ከተማ የተገነባ የዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ምርቃት ላይ ትላንት አርብ ታህሳስ 14፤ 2015 ባደረጉት ንግግር ነው። መንግስታቸው ሌብነትን ለመታገል በመነሳቱ፤ “ዋልታ የረገጡ ቡድኖችን” በመጠቀም “ኢትዮጵያን የማመስ” ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉ አካላት ለእነዚህ ኃይሎች “የፋይናንስ ድጋፍ” በመስጠት፤ “የሚያስተባብራቸውን ጉልበት” እንዲያገኙ እንዳደረጓቸው አብይ ገልጸዋል። “ሌብነት ሩቅ አይደለም፤ ጉያችን ስር ነው ያለው። ጉያችን ስር ያለው ሌብነት እነማንን ቢያስተባብር፤ ትኩረታችንን፣ ስራችንን ለማጨናገፍ እንደሚችል ያውቃል። አሁን የምታዩት ነውጥ ሁሉ ‘የሌብነት ዘመቻው ይቁም’ የሚል ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስታቸው በሙሰኞ ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር በመጀመሪያ ያስታወቁት ከሶስት ወር ገደማ በፊት ከወጣቶች ጋር በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት ላይ ነበር። ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ደግሞ በሙስና ላይ የሚከፈተውን ዘመቻ የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተካተቱበት ሰባት አባላት ያሉበት ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ፤ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም የሙስና ተዋንያን የሚለይ እና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል። ይህንኑ ተከትሎም፤ ተመሳሳይ ኃላፊነት የተጣለባቸው ክልላዊ ኮሚቴዎች በክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸው ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትላንቱ ንግግራቸው “ኢትዮጵያ ሌብነትን በፍጥነት እና በኃይል ካልተዋጋች በስተቀር ብልጽግናዋን ልታረጋግጥ አትችልም። ብልጽግና ካልተረጋገጠ ደግሞ የተራበ 120 ሚሊዮን ዜጋ ሆኖ ሀገሩን ሊጠብቅ፣ ሊታደግ አይችልም” ሲሉ በሙስና ላይ የተጀመረው ዘመቻን አስፈላጊነት አስረድተዋል። “ዜጎቻችንን ለማብላት ስንል አብዝተን ልማት ላይ እንሰራለን፤ አብዝተን ሌብነትን እንጠየፋለን” ሲሉም አክለዋል።
“ኢትዮጵያ የሌብነት ዘመቻዋን አጠናክራ ካልቀጠለች፤ በሌላ መንገድ የሚገጥማት ፈተና በሌብነቱም ስለሚገጥማት፤ ሌብነት መታገልን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ አብይ የመንግስታቸውን አቋም አስታውቀዋል። “ብር አጭቀን ስለያዝን፣ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ መቅጠር ስለምንችል፣ 10 እና 20 ወጣት አስታጥቀን ሰው መግደል ስለምንችል ‘የሌብነት ዘመቻው’ ይቆማል ብላችሁ የምታስቡ ግን ሞኛ ሞኞች ናችሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ከዚህ ቀደም በሙስና ገንዘብ ለሰበሰቡ ሰዎችም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ቀላል” ያሉትን መፍትሔ በትላንቱ ንግግራቸው ጠቁመዋል። “ትላንትና ተሳሳታችሁ በስህተት ሰርቃችሁ ሀብት ያከማቻችሁ ሰዎች ካላችሁ፤ መፍትሔው ቀላል ነው። ብዙ ዳቦ ፋብሪካ ስለምንፈልግ፣ ብዙ ትምህርት ቤት ስለምንፈልግ፤ ፋብሪካዎቹን ከሰራችሁ ሰላም ይመጣል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“ብር አይምጣ አይደለም። ብር ሊመጣ ይችላል፤ በሎተሪም፣ በስጦታም። ያንን ብር ግን ለህዝብ ጥቅም የምናውለው ከሆነ አያጣላንም። ያ የሚገኝ ገንዘብ ለውስኪ እና ለግል ጥቅም እየዋለ፤ ‘ኢትዮጵያን በማመስ፣ ቤትን ብቻ ማደስ’ የሚያስቡ ሰዎች እንደዚህ አይነት ዘመን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስተናገድ ስለማንችል ዘመቻው ይቀጥላል” ሲሉም መንግስታቸው የጀመረውን የጸረ-ሙስና ዘመቻ እንደሚገፋበት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)