የትግራይ ክልል ካቢኔ ቀዳሚ የቤት ስራ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ማስፈጸም ነው” – ረዳኢ ሓለፎም 

በአማኑኤል ይልቃል

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የመጀመሪያ ተግባር “የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ማስፈጸም እና መፈጸም” መሆኑን የትግራይ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ዛሬ በይፋ ኃላፊነቱን የተረከበው እና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ካቢኔ ዋና ትኩረት፤ “ፖለቲካዊ፣ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል”  እንደሚሆን ኃላፊው አስረድተዋል።

አቶ ረዳኢ ክልሉ ለገጠመው አንገብጋቢ ሰብዓዊ ቀውሶች መፍትሔ መሻት፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጨማሪ ኃላፊነት እንደሚሆንም ገልጸዋል። “አሁንም ቢሆን በሌሎች ኃይሎች እጅ የወደቀ የትግራይ ህዝብ አለ። ወደ ቀዬው ያልተመለሰ ብዙ ተፈናቃይ አለ። በቂ ምግብ እና መድኃኒት ያላገኘ ብዙ የትግራይ [ህዝብ አለ]” ሲሉም የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የካቢኔውን ቀጣይ ስራዎች ጠቁመዋል።

ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 27 የካቢኔ አባላት መካከል፤ ስምንት ኃላፊዎች በካቢኔ ሴክሬተሪያትነት የተሾሙ ናቸው። በካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊነት ከተሾሙት ስምንት ግለሰቦች ውስጥ፤ አቶ በየነ ምክሩ፣ ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት እና ወይዘሮ ያለም ጸጋይ የህወሓት አመራሮች ናቸው። 

ከትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው በተጨማሪ የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊነትን የተሾሙት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የሆኑት ብርጋዴየር ጄኔራል ተኽላይ አሸብር ከትግራይ ኃይሎች የተወከሉ ናቸው። በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እንዲሁም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ እና ስልጠና ሴክሬተሪያት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አልጋነሽ ተሰማ ምሁራንን በመወከል የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔውን የተቀላቀሉ ናቸው።

ስምንቱ የካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊዎች፤ በስራቸው የሚይዟቸውን ቢሮዎች ስራ የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያላቸው እንደሆኑ አቶ ረዳኢ ተናግረዋል። “ሁሉም አጠቃላይ ካቢኔ ወደ ርዕሰ መስተዳድር ከሚሆን፤ ለስራ ክትትል፣ ለቅልጥፍና፣ ለጊዜም ተብሎ ሰብሰብ ብለው የእቅድ ድጋፍ እንዲያገኙ የተሰራ አደረጃጀት ነው” ሲሉ ካቢኔ ሴክሬተሪያት የተባለው መዋቅር የተዘረጋበትን ምክንያት አቶ ረዳኢ አብራርተዋል። 

ይሁንና እነዚህን የካቢኔ ሴክሬተሪያት የሚመሩት ኃላፊዎች፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ በሚያሳልፍበት ጊዜ የሚኖራቸው ድምጽ “ከሚከታተሏቸው ቢሮዎች ኃላፊዎች ጋር እኩል ይሆናል” ብለዋል። በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተደራጁት እነዚህ መዋቅሮች በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ ቢጀምሩም፤ የቢሮዎቹ ኃላፊዎች ከቀድሞ አመራሮች ጋር የሚያደርጉት ርክክብ በቀጣይነት ይጠበቃል። ከቀድሞ የትግራይ ክልል መንግስት ካቢኔ አባላት ጋር በዛሬው ዕለት የተደረገው ርክክብ፤ አዲሱ ካቢኔ በይፋ ኃላፊነቱን መረከቡን ለማሳየት የተከናወነ ስነ ስርዓት መሆኑንም አቶ ረዳኢ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)