ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ አራት የ“ቴሌ ብር” ብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶችን ይፋ አደረጉ

በአማኑኤል ይልቃል

ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ በቴሌ ብር የሚከወኑ አራት የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በጋራ አስጀመሩ፡፡ ሁለት ተቋማት ባስጀመሯቸው አዳዲስ አገልግሎቶች፤ እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ ብድር ያለ ማስያዣ እንደሚያበድሩ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የቴክኖሎጂ እና በንግድ ባንክ የፋይናንስ አቅራቢነት ተዘጋጅተዋል የተባሉት አገልግሎቶች ይፋ የተደረጉት ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 20፤ 2015 ነው፡፡ ሁለቱ መንግስታዊ የቴሌኮሚዩኒኬሽን እና የፋይናንስ ተቋማት ትላንት ካስጀመሯቸው አራት አገልግሎቶች ውስጥ ሶስቱ ብድር የሚሰጥባቸው ሲሆኑ አንዱ ደግሞ ለቁጠባ የሚያገለግል ነው፡፡

“ስንቅ” የሚል ስያሜ የተሰጠው አገልግሎት፤ አነስተኛ ቁጠባዎችን ለማግኘት የሚውል ሲሆን “ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ ምጣኔየሚታሰብበትን” ገንዘብ ለመቆጠብ እንደሚያስችል በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባው ስካይት ላይት ሆቴል በተደረገው ስነ ስርዓት ላይ ተጠቅሷል፡፡ ሁለተኛው አገልግሎት ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌ ብር ለሚፈጸምላቸው ግለሰቦች አልያም የሰራተኞቻቸውን ደመወዝ በቴሌብር ለሚከፍሉ ተቋማት ብድር የሚሰጥበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

“አድራሽ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አገልግሎት፤ ሰራተኞች “ለደመዝ መዳረሻ” የሚሆናቸውን እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ ብድር የሚያገኙበት ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያበድር የተገለጸው ሌላኛው አገልግሎት ደግሞ ለነጋዴዎች እና ወኪሎች የቀረበ ነው፡፡ “ድልድይ” የሚል ስያሜ ባገኘው ይህ አገልግሎት፤ ብድር የሚያገኙት “አነስተኛ ንግድ ለመጀመር ወይም ለማስፋፋት” የሚፈልጉ ተበዳሪዎች ናቸው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እና ንግድ ባንክ ይፋ ያደረጉት አራተኛው አገልግሎት፤ ደንበኞች በቴሌብር አማካኝነት በሚያከናውኑት የግብይት መጠን ልክ ብድር የሚያገኙበት ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው ትልቁ ብድር 15 ሺህ ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ያለ ማስያዣ የሚሰጡት እነዚህ የአነስተኛ ብድር አገልግሎቶች፤ ከአስር ቀን እስከ አራት ወር የሚቆይ የመመለሻ ጊዜ ቆይታ እንዳላቸው በትላንቱ ስነ ስርዓት ላይ ተጠቅሷል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)