ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እገዛ እንድታገኝ፤ የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናገሩ 

የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ካሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚፈልገውን እገዛ እንዲያገኝ፤ የአሜሪካ መንግስት ጠንካራ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። መንግስት በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል “የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ” የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መንግስት በቅርቡ “ጠንካራ አቋሙን” እንደገለጸ የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል። 

አቶ አህመድ ይህን የተናገሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለ2016 በተዘጋጀው የበጀት ረቂቅ ላይ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 27፤ 2015 ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። “ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት እጅግ የተሻለ” ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በዚሁ ማብራሪያቸው የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የአውሮፓ ህብረት የልማት እርዳታ ሊቀጥል እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

ህብረቱ ለኢትዮጵያ የልማት እርዳታ የሚሰጥበትን “multi-annual development program” እንደገና ለማስጀመር “ከጥቂት ወራት በኋላ” ስምምነት እንደሚፈረም አቶ አህመድ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ አጋሮች የሚጠብቀው እገዛ በበጀት ረቂቁ ውስጥ እንዳልተካተተ ያረጋገጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ ይሁንና መንግስታቸው “የተሻለ ሁኔታ እንደሚኖር” ተስፋ ማድረጉን በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ከአሜሪካ እና አውሮፓ ጋር ያለው ግንኙነት በጦርነት ምክንያት ሻክሮ የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት፤ በ2015 ከውጭ ቀጥታ የበጀት ድጋፍ ለማግኘት አቅዶ የነበረውን 7.7 ቢሊዮን ብር ሳያገኝ መቅረቱን አቶ አህመድ ባለፈው ግንቦት ወር ለፓርላማው መግለጻቸው ይታወሳል። የገንዘብ ሚኒስትሩ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያቸው፤ አሜሪካ እና አውሮፓን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮቿ ጋር ያላት ግንኙነት መሻሻል ለሚቀጥለው ዓመት በጀት ይዞት የሚመጣው ትሩፋት እንደሚኖር ተስፋቸውን አጋርተዋል። 

የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛ ምዕራፍን ሊያግዙ ከሚችሉ የልማት አጋሮች ጋር፤ መንግስት የሚያካሄዳቸው “ውይይቶች በጣም አዎንታዊ” መሆናቸውንም አቶ አህመድ ጨምረው ገልጸዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ የዛሬው ማብራሪያ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግስት ይፋ ያደረገው ውሳኔ፤ በኢትዮጵያ መንግስት ዘንድ የፈጠረውን አዎንታዊ ተስፋን የሚጠቁም ነው። የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ታይተዋል ያላቸውን መሻሻሎች መሰረት በማድረግ፤ የተወሰኑ ገደቦች ማንሳቱን ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም። 

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ስትሰጥ የቆየችውን የምግብ እርዳታ “በስርጭት ወቅት ተፈጽሟል በተባለ ስርቆት” ምክንያት ማቆሟን የዛሬው ወር ገደማ ይፋ ብታደርግም፤ የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሀገራቸው በአንዳንድ የእርዳታ አይነቶች ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ እንዳነሳች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን “ሮይተርስ” ዘግቧል። ቃል አቀባዩ በዚሁ ንግግራቸው “ይህ ውሳኔ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የምናደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር የሚያስፈልጉንን አማራጮች ያሰፋል” ማለታቸውንም የዜና ወኪሉ አክሏል።

የአሜሪካ የአሁኑ ውሳኔ፤ ኢትዮጵያ እንደ አይ ኤም ኤፍ ካሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር እና እርዳታ እንዳታገኝ ስትከተል የቆየችውን አቋም የሚቀይር ነው። አሜሪካ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብቻ ከ16 በመቶ በላይ ድምጽ አላት። ኢትዮጵያ ከተቋሙ የጠየቀችው ጠቀም ያለ ብድር እንዲጸድቅ፤ እንደ አሜሪካ ያሉ ልዕለ ኃያላን ሀገራት ድምጽ በሚሰጡበት አስተዳደር ቦርድ መጽደቅ ይኖርበታል። 

አሜሪካ ተቋርጦ የነበረውን የሁለትዮሽ ድጋፍ እንደገና የምትጀምረው፤ የግጭት ማቆም ስምምነቱን አተገባበር በማገዝ ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሆነ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ መናገራቸውን “ሮይተርስ” ከቀናት በፊት ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። ውሳኔው ፈንጂዎችን በማስወገድ፣ የሽግግር ፍትህ እና ተጠያቂነትን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላም እና እርቅን የማበረታታት ዓላማ ጭምር ያነገበ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ በሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ረገድ ያለውን ስጋት አሜሪካ ከመግለጽ እንደማትቆጠብ አስታውቀዋል ብሏል።

“በምዕራብ ትግራይ መንግስታዊ ባልሆኑ ወገኖች የሚፈጸመውን ጨምሮ ስለ ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የሚቀርቡ ሪፖርቶች ያሉንን ስጋቶች መናገራችንን እንቀጥላለን” ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቅ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ ሀገራቸው የምታሳድረው ግፊት እንደማይቆም መግለጻቸውንም የ“ሮይተርስ” ዘገባ ጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)