የቀድሞው የብአዴን ከፍተኛ አመራር አቶ ታደሰ ካሳ ከእስር ተለቀቁ 

በአማኑኤል ይልቃል

ለአራት ዓመት ተኩል በእስር ላይ የቆዩት የቀድሞው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከፍተኛ አመራር አቶ ታደሰ ካሳ ዛሬ ሐሙስ ከእስር መለቀቃቸውን ጠበቃቸው ህይወት ሊላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አቶ ታደሰ ከእስር የተለቀቁት፤ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በነጻ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ካስተላለፈ አንድ ሳምንት በኋላ ነው። 

ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተከስሰው የተፈረደባቸው አቶ ታደሰን በተመለከተ፤ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት በዋለው ችሎቱ ነበር። ችሎቱ ጉዳዩን የተመለከተው የአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ2012 ዓ.ም “ጥፋተኛ ናቸው” በማለት አቶ ታደሰ ላይ ያስተላለፈውን ቅጣት በተመለከተ በቀረበለት አቤቱታ መሰረት ነው።

አቶ ታደሰ የተከሰሱት በስራ አስፈጻሚነት ሲመሩት የነበረው ጥረት ኮርፖሬት፤ “በቂ ጥናት ሳይደረግ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ለመስራት ውል ገብቷል። በዚህም ድርጅቱ ጉዳት ደርሶበታል” በሚል ነበር። ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው የአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ አቶ ታደሰ ላይ የስምንት ዓመት ከአምስት ወራት እስር እንዲሁም የ15 ሺህ ብር መቀጮ ቅጣት አስተላልፎ ነበር። ይህ ቅጣት ከተላለፈ በኋላ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ሲጠየቅ መቆየቱን ጠበቃ ህይወት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

በሁለቱ የአማራ ክልል የፍርድ ቤት እርከኖች የቀረበው ጥያቄ ውድቅ በመሆኑ፤ ጉዳዩ በ2014 ዓ.ም ወደ ፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት መምጣቱን ጠበቃዋ አስታውሰዋል። የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት “መስተካከል አለባቸው ያላቸውን ነጥቦች ጠቅሶ ወደ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት” ጉዳዩን ቢመልስም፤ አቤቱታው በድጋሚ ውድቅ መደረጉን ህይወት ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ከአምስት ወራት በፊት አቤቱታው ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት እንደገና መቅረቡን አብራርተዋል። 

ከየካቲት ወር ጀምሮ ጉዳዩን በድጋሚ ሲመለከት የቆየው የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት፤ ባለፈው ሳምንት በዋለው ችሎቱ “የህግ ስህተት ተፈጽሟል” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ጠበቃዋ ተናግረዋል። ከአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጀምሮ በአቶ ታደሰ ላይ የተላለፉ የፍርድ ውሳኔዎች “ሙሉ በሙሉ እንዲሻሩ” እና ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዙን መስጠቱንም ገልጸዋል።

የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ትዕዛዙን ያስተላለፈው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ቢሆንም፤ አቶ ታደሰ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይለቀቁ ቆይተዋል። ደንበኛቸው እስከ ዛሬ ድረስ ሳይፈቱ የቆዩት፤ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት የታሰሩበት  የቃሊቲ ማረሚያ ቤት “በራሱ መልቀቅ ስለማይችል” እንደሆነ ጠበቃ ህይወት አስረድተዋል። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አብዛኛውን የእስር ጊዜያቸውን በባህር ዳር ማረሚያ ቤት ያሳለፉት አቶ ታደሰ፤ በህክምና ምክንያት በተዛወሩበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የቆዩት “በአደራ” ነበር።

አቶ ታደሰ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 13፤ 2015 ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት የተለቀቁት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ተኩል ገደማ እንደሆነ ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ደንበኛቸው ከእስር ከተፈቱ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)