በአፋር ክልል በትላንትናው ዕለት በደረሰ ጥቃት ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ  

በአፋር ክልል “የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸዋል” ከተባሉ እና ከአጎራባች አካባቢዎች ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከቀያቸው የተፈናቀሉት ነዋሪዎች፤ በአፋር ክልል፣ ዞን ሁለት፣ መጋሌ ወረዳ በሚገኘው በፋሮ ቀበሌ እና በአቅራቢያው በሚገኙ ቦታዎች መጠለላቸውንም ባለስልጣኑ ገልጸዋል።

በመጋሌ ወረዳ በሚገኘው ቶንሳ ቀበሌ ላይ ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 26፤ 2018 በህወሓት ቡድን ጥቃት መፈጸሙን የአፋር ክልል መንግስት ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው፤ የህወሓት ቡድን በዚሁ ቀበሌ የሚገኙ ስድስት አካባቢዎችን “በጉልበት ተቆጣጥሯል” ሲል ወንጅሏል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በስልክ ያነጋገረቻቸው ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንኑ የክልሉን መረጃ አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያሉ ቦታዎች ሚልኪ፣ ዋረዓ፣ ሚላ፣ ከረፈቱ፣ ካኦሶበራ እና ከረሙአጋ የተባሉ አካባቢዎች መሆናቸውን እነዚሁ ነዋሪዎች ገልጸዋል።  

የአፋር ክልል መንግስት በትላንቱ መግለጫው፤ ዋራዓ እና ሚልኪ በተባሉ ቦታዎች የህወሓት ቡድን በንጹሃን የአፋር አርብቶ አደሮች ላይ “የከባድ መሳሪያ ተኩስ ከፍቷል” ሲል ወንጅሎ ነበር። በእነዚህ አካባቢዎች በሞርታር እና በዙ-23 “ድብደባ” የተፈጸመው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ እንደነበርም በመግለጫው አመልክቷል። 

የቶንሳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አንድ የዓይን እማኝ፤ የትላንቱ የከባድ መሳሪያ ተኩሱ የቆየው ከአመሻሽ 12 ሰዓት ተኩል ገደማ ጀምሮ እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ተኩሱ ሲጀመር የአካባቢው ነዋሪዎች ከስፍራው በመሸሻቸው በሰዎች ላይ በርካታ ጉዳት አለመድረሱን አስረድተዋል። 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቶንሳ ቀበሌ የስራ ኃላፊ ባለስልጣን፤ አካባቢዎቹ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በመሆናቸው በጥቃቱ የደረሰውን ትክክለኛ ጉዳት ለማጣራት አለመቻሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም በጥቃቱ በእንስሳት እና በቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ሰምቻለሁ ብለዋል። 

በትላንቱ ጥቃት ሳቢያ ሰባት መቶ ገደማ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሚያሳይ መረጃ እንደደረሳቸውም የስራ ኃላፊው አክለዋል። የመጋሌ ወረዳ የእንስሳት፣ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው የትላንቱን ጥቃት ተከትሎ በሶስት ቀበሌዎች ነዋሪዎች የሆኑ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት ቶንሳ፣ ፋሮ እና አዱ ከተባሉ ቀበሌዎች መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል። ከቶንሳ ቀበሌ ብቻ 1,333 አባወራዎች እና እማወራዎች መፈናቀላቸውን የገለጹት አቶ አብዱ፤ ከአዱ 786 እና ከፋሮ 660 አባወራዎች በተመሳሳይ መኖሪያቸውን ለቀቅው ወደ ሌሎች ቦታዎች መሄዳቸውን አብራርተዋል።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙት በፋሮ ቀበሌ በሚገኙ አካባቢዎች እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አብዱ፤ ኢብሮ እና ሳፋዶሬ በተባሉ የቀበሌው ስፍራዎች ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ አሮሪ ወደ ተባለ ስፍራ የሄዱ ተፈናቃዮች እንዳሉም አክለዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረችው አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ “የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረውታል” በተባለ ቦታ ያሉ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቅቀው ለመሄድ ሲሞክሩ ክልከላ እንደተደረገባቸው መስማቱን ገልጿል። በእነዚህ አካባቢዎች እህቶቹ እና ወንድሞቹ እንደሚገኙ ያመለከተው ይሄው ግለሰብ፤ እነርሱን በስልክ ባነጋገረበት ወቅት በነዋሪዎች ላይ ድብደባ እየተፈጸመ መሆኑን እንደገለጹለት አስረድቷል። 

ይኸው ነዋሪ በእነርሱ አካባቢ “የትግራይ የሰላም ኃይሎች” የሚባሉ ታጣቂዎች ላለፉት አራት ወራት ሲንቀሳቀሱ መመልከቱን ገልጿል። “ህወሓቶች” ወደ አካባቢው የመጡት እነዚህን ኃይሎች ለማጥቃት ነው የሚል ግምቱን አስቀምጧል። በዛሬው ዕለት እስከ እኩለ ቀን ድረስ በአካባቢው ምንም አይነት የተለየ እንቅስቃሴ አለመኖሩንም የዓይን እማኝነቱን ሰጥቷል።

የትላንቱ ጥቃት ሲፈጸም ከቀያቸው አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት በሚገኝ ስፍራ ሆነው የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ያመለከቱት ሌላ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከዚያ በኋላ ወደ መኖሪያቸው መመለስ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ባለቤታቸው እና ልጃቸው በእነዚህ አካባቢዎች እንዳሉ የገለጹት እኚሁ ነዋሪ፤ በዛሬው ዕለት ተጨማሪ “ህወሓቶች” ወደ አካባቢው መምጣታቸውን ተናግረዋል። 

የአፋር ክልል መንግስት ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ “የህወሓት ቡድን” የክልሉን ወሰን ተሻግሮ ከፈጸመው ድርጊት “በአስቸኳይ እንዲቆጠብ” አሳስቦ ነበር። ቡድኑ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ግን የክልሉ መንግስት “የዜጎች ደህንነትና የወሰኑን ክብር የማስጠበቅ”፣ እንዲሁም ራሱን “ከማንኛውም ውጫዊ ጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ” አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)