የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን የሚከታተለው የባለሙያዎች ቡድን ከእረፍት በኋላ ወደ ትግራይ ተመለሰ  

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ስምምነት አተገባበር የሚከታተለው የባለሙያዎች ቡድን፤ ከ“እረፍት በኋላ” ዳግም ለስራ መሰማራቱን የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ። የባለሙያዎች ቡድኑ የስምምነቱን አፈጻጸም የመከታተል “ወሳኝ ተግባራቸውን” እንደገና ጀምረዋል ብሏል።

የአፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም የመከታተል እና የማረጋገጥ ኃላፊነት የተሰጠውን ተልዕኮ ይፋ ያደረገው በታህሳስ 2015 ዓ.ም ነበር። በዚህ ተልዕኮ ስር የተካተቱ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የተውጣጡ 21 ወታደራዊ እና የሲቪል ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። 

ባለሙያዎቹ ቁጥጥር ከሚያደርጉባቸው ሂደቶች መካከል በውጊያ ሲሳተፉ የነበሩ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት፣ እንዲበተኑ ማድረግ እና ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ ማዋሃድን የሚመለከተው አንዱ ነው። ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሰዎች መልሶ ማስፈር፣ የኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ዳግም መጀመር፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ማመቻቸት እና የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ማስጠበቅን የተመለከቱ ጉዳዮችም ባለሙያዎቹ የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

እነዚህን ጉዳዮች ለመከታተል በትግራይ ክልል ተሰማርቶ የቆየው የአፍሪካውያን የባለሙያዎች ቡድን፤ “የአስተዳደር እረፍት” ወስዶ እንደነበር የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ዛሬ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። የባለሙያዎቹ ቡድኑ ከእረፍት በኋላ በዛሬው ዕለት ወደ ስምሪት መመለሱን ቢሮው በፎቶዎች አስደግፎ አስታውቋል።

ቢሮው በኤክስ ገጽ ያጋራቸው ፎቶዎች፤ አምስት የቡድኑ አባላት መቐለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ መድረሳቸውን ያሳያል። ባለሙያዎቹ ትግራይ የገቡት፤ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ “የፕሪቶሪያ ስምምነት ተጥሷል” የሚሉ ስሞታዎች መቅረባቸውን ተከትሎ ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈረም ቁልፍ ሚና የተጫወተው የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ ከሰሞኑ የተፈጠሩ ግጭቶች እንዳሳሰባቸው ገልጸው ሁሉም አካላት ሁኔታውን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ ጥሪ አቅርበው ነበር። የተፈጠሩት ችግሮች በህብረቱ አደራዳሪነት በተካሄደው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መርህ አማካኝነት ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው አመልክተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)