ፖሊስ ሁለት የኢህአፓ አባላትን እና የፓርቲውን ጠበቃ “የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ወነጀለ   

ከትላንት በስቲያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሁለት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አባላት እና የፓርቲው ጠበቃ፤ “የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል” የሚል ውንጀላ ቀረበባቸው። ፖለቲከኞቹ እና ጠበቃው ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት (ህወሓት)፣ “ከሌሎች ጸረ- ሰላም ኃይሎች” እና “ጽምዶ” ተብሎ ከሚጠራው ኃይል ጋር “በመቀናጀት” በአዲስ አበባ ከተማ አባላትን “በመመልመል” እና “በማደራጀት” ተጠርጥረዋል። 

የፌደራል ፖሊስ እነዚህን ውንጀላዎች ያቀረበው፤ በአቶ አበበ አካሉ፣ አቶ ይስሀቅ ወልዳይ እና አቶ አበራ ንጉስ ላይ ነው። የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ይስሀቅ እና የህግ ባለሙያው አቶ አበራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሐምሌ 27 እንደሆነ ፓርቲያቸው በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አቶ አበበ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፓርቲው ያረጋገጠው ደግሞ በትላንትናው ዕለት ነው። የፌደራል ፖሊስ ሶስቱንም ተጠርጣሪዎች ከትላንት በስቲያ እና ትላንት በእጀባ ወደ መኖሪያ ቤቶቻቸው በመውሰድ ፍተሻ ማካሄዱን እና የተወሰኑ ቁሳቁሶችን ይዞ መሄዱን ቤተሰቦቻቸው እና የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 29፤ 2018 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት መቅረባቸውን የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ምስጢረ ሥላሴ ታምራት እና ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። በዛሬው የችሎት ውሎ የፌደራል ፖሊስ የ14 ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።  

ፖሊስ የምርመራ ጊዜ ለመጠየቅ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ማመልከቻ፤ ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የህግ ባለሙያው የተጠረጠሩባቸውን ወንጀሎች የዘርዘረ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይኸው ማመልከቻ፤ ሶስቱ ተጠርጣሪዎች “ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን እንደ ሽፋን በመጠቀም ከፓርቲው ህግ እና አላማ ውጪ ስልጣን በኃይል ለመያዝ በማሰብ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ተወንጅለዋል።

ግለሰቦቹ ይህንኑ ሃሳባቸውን ለማሳካት ሃሳብ ከ“ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች” መቀናጀታቸውም በማመልከቻው ላይ ተጠቅሷል። በፖሊስ ማመልከቻ “በጠላትነት” ተፈርጀው የተዘረዘሩት ህወሓት፣ “ጽምዶ” ተብሎ የሚጠራው ኃይል እና ስማቸው ያልተጠቀሱ “ሌሎች ጸረ ሰላም ኃይሎች” ናቸው።

“ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በድብቅ ግንኙነት በማድረግ” የተጠረጠሩት ሶስቱ ግለሰቦች፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመንቀሳቀስ “አባላትን እና በመልመልና በማደራጀት”፣ የጸጥታ ኃይሎችን እንቅስቃሴ “በመሰለል” እና “ለጽምዶ ቡድን መረጃ በማቀበል” ተወንጅለዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች እና ጠበቃው “ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የፖለቲካ ክንፍ፣ የወታደራዊ አደረጃጀትና ስልጠና ክንፍ፣ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ክንፍ እና ሌሎች የድርጊት መርሃ ግብር አፈጻጸም በማውጣት” መንቀሳቀሳቸውንም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።

ግለሰቦቹ “ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ‘በኃይልም ቢሆን ማስወገድ አለብን’፣ ‘በየትኛውም አካባቢ የሚደረግ የትጥቅ ትግል አግባብ ነው’ በማለት”፣  “ለህዝቡ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ አማራጭ መሆን እንዳለበት” መናገራቸውን ፖሊስ በማመልከቻው ላይ ጠቅሷል። ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በችሎት በነበራቸው ቆይታ፤ ይህን በተመለከተ የቀረበባቸውን ውንጀላ ማስተባበላቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ “ሰላማዊ ትግል ነው የምናምነው። መንግስትን በኃይል የመገልበጥ እሳቤ የለንም” ማለታቸውን አቶ ሰለሞን አክለዋል። “መንግስት እንዲስተካከል የሚጥሩ” መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ የገለጹት አቶ አበበ፤ “ሀገር አለኝ፣ ልጆች አሉኝ። በሰላማዊ ትግል ነው የምናምነው” ማለታቸውን ጠበቃቸው አስረድተዋል። 

የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻ ላይ ተጠርጣሪዎቹ “የብሔር እና የሃይማኖት ግጭትን ለመፍጠር በማሰብ” በውጭ ሀገር በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን “የሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጩ ነበር” በሚልም በተጨማሪነት ወንጅሏቸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በማመልከቻ ላይ በስም የጠቀሳቸው አንከር ሚዲያ፣ ኢትዮ ፎረም እና ኢትዮ 360 መገናኛ ብዙሃንን ነው።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ላይ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተቋማት እና በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ላይ “የሽብር ጥቃት ለመፈጸም” “በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ” እንደሆነ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገልጿል። ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ድርጊት “የሽብር ወንጀል ድርጊት” ከመሆኑ አንጻር እና ጉዳዩ “ውስብስብ” እና “ሰፊ ጊዜ” የሚያስፈልግ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ የጠቀሰው፤ የምርመራ ስራ ለማካሄድ 14 ቀናትን ጠይቋል።

የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ “ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ከእስር ቢለቀቁ ምስክሮችን ሊያሸሹብን፣ ሊያስፈራሩብን እና ሊደልሉብን ይችላሉ” በምክንያት በምርመራው ወቅት በእስር ላይ እንዲቆዩ ጥያቄ አቅርቧል። የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ለመመልከት ችሎቱ ለዛሬ ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል።

ችሎቱ በከሰዓቱ ውሎው፤ ፖሊስ ግለሰቦቹን በሽብርተኝነት የጠረጠረበትን በመገናኛ ብዙሃን የተላለፉ መልዕክቶች የሽብር ክስ እንደሚያቋቁም ለመረዳት እና በዋስትናው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ገልጿል። በዚህም መሰረት ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በመገናኛ ብዙሃን አድርገውታል የተባለውን ንግግር በማስረጃነት ይዞ ለነገ ሐሙስ ሐምሌ 30፤ 2018 እንዲቀርብ አዝዟል። 

ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎቹን መርምሮ በዋስትና ጥያቄው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ በስቲያ አርብ ነሐሴ 1 ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]