በተስፋለም ወልደየስ
በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በተለምዶ ዶሮ ማነቂያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የሚገኙ ነዋሪዎች፤ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከስፍራው እንዲነሱ ቀነ ገደብ ተሰጣቸው። የከተማይቱ አስተዳደር ምትክ የመኖሪያ እና የንግድ ቦታ ሳያዘጋጅላቸው፤ ከስፍራው “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ተነሱ ማለቱ በነዋሪዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦበታል።
ነዋሪዎቹ ይህን ቅሬታቸውን ያሰሙት፤ የአካባቢውን መልሶ ማልማት በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከአራዳ ክፍለ ከተማ የስራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ረቡዕ የካቲት 20፤ 2016 ባደረጉት ውይይት ነው። የዛሬው ውይይት የተጠራው፤ የፒያሳና አራት ኪሎ አካባቢ መልሶ የማልማት ፕሮጀክትን በተመለከተ በትላንትናው ዕለት በወረዳ ደረጃ የተደረጉ ውይይቶች “በአለመግባባት” እና “በረብሻ” መበተናቸውን ተከትሎ ነው።
በትላንትናው ውይይት ከ700 የሚልቁ ነዋሪዎች መሳተፋቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። በውይይቶቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እና በቂ መረጃ ባለማግኘት ለተፈጠሩ አለመግባባቶች፤ የአካባቢው አስተዳደር የዛሬውን ስብሰባ ማዘጋጀቱ ተገልጿል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ከንጋቱ 12 ሰዓት ተኩል ጀምሮ አዳራሽ ይካሄዳል ለተባለው የዛሬው ስብሰባ፤ በሺህ የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በቅርቡ በተመረቀው የአድዋ ድል መታሰቢያ መሰብሰቢያ አዳራሽ በማለዳ ተገኝተው ነበር።
በተባለው ጊዜ ሳይጀመር ለሁለት ሰዓት ያህል የዘገየው የዛሬው ስብሰባ፤ ቪዲዮ ለማሳየት በተፈጠረ “የቴክኒክ ችግር” ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ባህል አዳራሽ እንዲዛወር ተደርጓል። ስብሰባውን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ጥላሁን ወርቁ፤ የአካባቢውን መልሶ ማልማት በተመለከተ ጥናት ላካሄዱ ባለሙያ ገለጻ እንዲያደርጉ ዕድል ሰጥተዋቸዋል።
“ኮምፓስ” ከተሰኘ አማካሪ ድርጅት የመጡት ባለሙያ፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን የሚጎራበቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት የተያዘውን እቅድ በመጀመሪያ አቅርበዋል። በመልሶ ማልማቱ ዕቅድ የተካተተው አካባቢ “በመሀል ከተማ የሚገኝ ለኑሮ የማይመች መሆኑን” የጠቀሱት ባለሙያው፤ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር በጀመረው እንቅስቃሴ “ቅድሚያ ከተሰጣቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ” መሆኑን አስረድተዋል።
ባለሙያው በአኔሜሽን ቪድዮ አስደግፈው ባቀረቡት የከተማይቱ ዕቅድ፤ በአካባቢው ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ሱቆች፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ የትራንስፖርት ተርሚናል እና ሌሎች አገልግሎት መስጪያዎች ይገነባሉ። በተመሳሳይ መልኩ በቪዲዮ ታግዞ የቀረበው ሁለተኛው የከተማይቱ ዕቅድ፤ የአራት ኪሎ ኮሪደር ልማት ምን እንደሚመስል በወፍ በረር ያሳየ ነው። ይህ የልማት እቅድ አስተዳደሩ እያካሄደ ካለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር በተናበበ ሁኔታ የሚካሄድ መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል።
ከአራት ኪሎ እስከ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ያለውን መንገድ የሚከተለው ይህ ኮሪደር፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያጸደቀው ግዙፍ የመንገድ ልማት ፕሮጀክት አካል ነው። የመንገድ ኮሪደር ፕሮጀክቶቹ “አዋሳኝ የወንዝ ተፋሰሶችን ያቀፉ፣ የሳይክልና ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የከተማዋን ማስተር ፕላን እና urban ዲዛይን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሁም ለከተማዋ እጅግ ዘመናዊ የትራንስፖርት ፍሰት የሚያጎናጽፉ መሆኑ እንደታመነበት” የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
በዚህ ፕሮጀክት እንዲለሙ ዕቅድ ከተያዘላቸው አራት ኮሪደሮች መካከል ሁለቱ ከፒያሳ ጋር የተገናኙ ናቸው። ከፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ ተነስቶ በለገሃር፣ ሜክሲኮ፣ በሳርቤት በኩል እስከ ወሎ ሰፈር ያለው የመጀመሪያው ኮሪደር 10 ኪሎ ሜትር መንገድ ርቀት ያለው ነው። ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ በኩል እስከ አድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ድረስ ያለው ሌላኛው ኮሪደር ደግሞ 6.4 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው።
አስፈላጊ በሆኑ በእነዚህ የኮሪደር ቦታዎች ላይ “ደረጃቸውን የጠበቁ ተሸጋጋሪ ድልድዮች፣ ማሳለጫዎች እና ሰፋፊ መጋቢ መንገዶች” እንደሚገነቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጿል። “የከተማ አረንጓዴ ልማትን ያካተተ” የተባለለት ይህ የመንገድ ኮሪደር ፕሮጀክት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከጸደቀ ማግስት ጀምሮ “ወደ ስራ እንዲገባ እና ልዩ ክትትል እንዲደረግለት” ውሳኔ ተላልፎ ነበር።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሚመሩት ኮሚቴ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግለት የተነገረለት ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ያለው ኮሪደር ግንባታ አንድ ክፍል ትላንት ማክሰኞ የካቲት 19፤ 2016 መጀመሩን የአራዳ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል። በአራት ኪሎ አካባቢ የተጀመረው ይህ ግንባታ፤ ፕሮጀክቱ “በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት” የተደረገ መሆኑን የቢሮው መረጃ አመልክቷል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ ባሉ ወረዳዎች በትላንትናው ላይ በተካሄደው ውይይት ተሳታፊ በነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ “ከፍተኛ ቅሬታ” ፈጥሮ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ፤ “ፕሮጀክቱ በፍጥነት ይገነባል” መባሉ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ከሚኖሩበት እና ከሚነግዱበት ቦታ “በሶስት ቀናት ውስጥ እንዲለቅቁ” በውይይቱ ላይ ከተነገራቸው በኋላ “ረብሻ” መፈጠሩን ተናግረዋል። በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ እናቶች በውሳኔ በማዘን ሲያለቅሱ እንደነበር በስፍራው የነበሩት ገልጸዋል።
በዛሬው ውይይት ላይ ጥያቄ የማቅረብ ዕድል የተሰጣቸው ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ለከተማይቱ ባለስልጣናት ጥያቄ አቅርበዋል። በፒያሳ አካባቢ በአክሲዮን የተደራጁ ነዋሪዎች ማህበርን በሰብሳቢነት የሚመሩ ግለሰብ፤ “ቤት ለመቀባት እንኳ ሶስት ቀናት ይበቃል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ትላንት በነበሩ ውይይቶች ይህንን ውሳኔ የሰሙ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ለሊቱን ሙሉ ሳይተኙ ማደራቸውን እና አሁንም በስጋት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አምስት አባላት ያሉት ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን የገለጹ አንድ እናት፤ አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ እርሳቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በስፍራው የታቀደው የመልሶ ማልማት እነዚህን ነዋሪዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ምትክ የመኖሪያ ስፍራ ያዘጋጀ ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።
ይህንኑ ሃሳብ የተጋሩት ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለልማት ተነሺዎች የሚያዘጋጀው አማራጭ የስፍራውን “ማህበራዊ ትስስር” በማይበጥስ መልኩ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እርስ በእርስ ተደጋግፈው የሚኖሩ በመሆናቸው፤ ምትክ የኮንዶሚኒየም ቤት የሚሰጣቸው ከሆነ በአንድ ቦታ ላይ የሚሰፍሩበት ሁኔታ እንደሚቻችላቸው ጠይቀዋል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ ከሰጡ ባለስልጣናት አንዱ የሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጥላሁን፤ የከተማይቱ አስተዳደር ነዋሪዎቹን ከቦታው ለማንሳት ያቀደው በዘጠና ቀናት ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል። አስተዳደሩ ለነዋሪዎች ምትክ የኮንዶሚኒየም፣ የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶች እንደሚያዘጋጅ ቃል ገብተዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ተቀባ በበኩላቸው፤ የከተማይቱ አስተዳደር “ቅደመ ሁኔታ ሳያሟላ አንድም ሰው አይነቃነቅም” ሲሉ ለነዋሪዎቹ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የከተማው አስተዳደር “ቅደመ ሁኔታውን ካሟላ” ነዋሪዎች በሶስት ቀን ቢነሱ ችግር እንደማይፈጥርም ጠቁመዋል። “ይህ ፕሮጀክት እንዳያልቅ የሚያንጓትት ካለ ኃላፊነቱን ራሱ ነው የሚወስደው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በዛሬው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በመልሶ ማልማቱ የልማት ተነሺዎቹን ሂደት የሚከታተል ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተከናውኗል። በመልሶ ማልማት እቅዱ የተካተተውን የፒያሳ አካባቢን በስድስት በመክፈል፤ ከእያንዳንዱ ስፍራ ስድስት ሰዎች በህዝብ ተመርጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)