የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው። ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዛምቢያ የሚያደርጉት ጉብኝት፤ አሜሪካ ከየሀገራቱ ጋር ያላትን “ቁልፍ” የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የማጠናከር እንዲሁም የጸጥታ እና የኢኮኖሚ አጋርነቶችን የማሳደግ ዓላማ ያለው ነው ተብሏል።

ጋርሺያ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በነገው ዕለት ሶስተኛ ወር ይሞላቸዋል። በአሜሪካ ባህር ኃይል ለ28 ዓመታት ያገለገሉት ጋርሺያ፤ ለአንድ ዓመት ክፍት ሆኖ የቆየውን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት በሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደህንነት ጉዳዮች ኮሚቴ ከፍተኛ አማካሪ እና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል።

በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ የአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጉ የነበሩት ጋርሺያ፤ ወደ አህጉሪቱ ከሚጓዙ ልዑካን ጋር በርካታ ጉብኝቶች የማድረግ ዕድል አጋጥሟቸዋል። የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሹመት ካገኙ በኋላም ጉብኝታቸውን አላቋረጡም።

ጋርሺያ ረዳት ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ያደረጉት በምዕራብ አፍሪካ ወደሚገኙት ናይጄሪያ፣ አይቮሪ ኮስት እና ማሊ ነበር። ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ የተደረገው የረዳት ሚኒስትሩ ጉብኝት በዋነኛነት ትኩረቱን ያደረገው አሜሪካ በቀጠናው ባለት የጸጥታ ጥቅሞች ላይ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል። 

ዩናይትድ ስቴትስ በምዕራብ አፍሪካ ከቻይና እና ሩሲያ ጋር እያጋጠማት ያለው እያደገ የመጣ ስትራቴጂካዊ ፉክክርም ሌላው ጉብኝቱ ያጠነጠነበት ጉዳይ ነበር። የምዕራብ አፍሪካው ጉብኝት ሌላኛው ዓላማ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን የማበረታት ጉዳይ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶስት ሀገራት በሚደረገው ጉብኝት አጀንዳ ላይም ተካትቷል።

የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትሩ ከአንድ ሳምንት በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሆኑት አቶ ብናልፍ አንዷለም ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም ይኸው የኢኮኖሚ ትብብር ጉዳይ ተነስቷል። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባሰራጨው መረጃ መሰረት፤ ብናልፍ እና ጋርሺያ ከተወያዩባቸው ኢኮኖሚያው ጉዳዮች መካከል “ወሳኝ የሆነው የማዕድን ዘርፍ” ይገኝበታል።

በአምባሳደሩ እና ረዳት ሚኒስትሩ ውይይት ወቅት የተነሳው ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ በምትገኝበት “ቀጠናው አካባቢ እየተስተዋሉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚከናወኑ የትብብር መስኮችን” የተመለከተ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል። ሁለቱ ዲፕሎማቶች በእነዚህ የትብብር መስኮች “በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን” ኤምባሲው ቢገልጽም፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የአሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና ዛምቢያ የሚያደርጉት ጉብኝት “ቁልፍ የጸጥታ አጋርነቶችን” የማጠናከር ዓላማ እንዳለው መስሪያ ቤታቸው ትላንት አርብ ለሊት ባወጣው መግለጫ ቢጠቅስም፤ በተመሳሳይ መልኩ ዝርዝር ጉዳዮችን ሳይጠቅስ ቀርቷል። በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ በትግራይ ክልል ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት አሳሳቢ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)