“የአንድ መጠነኛ ሀገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሳሪያ ሰራዊታችን ተቆጣጥሯል” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

መከላከያ ሰራዊት በምጽዋ ወደብ የተላለፈ፣ “የአንድ መጠነኛ ሀገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል የጦር መሳሪያ መቆጣጠሩን” የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ተናገሩ። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ በአባይ ውሃ እና በቀይ ባህር የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጥቅም “ከማስከበር ውጪ አማራጭ የለውም” ብለዋል።

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ይህንን ያሉት፤ ዛሬ እሁድ ጥቅምት 15፤ 2019 በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት የምስረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የመከላከያ ሰራዊት ምስረታ በዚህ ዕለት እንዲከበር የተደረገው፤ አጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያቋቋሙበት እና ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን የጦር ሚኒስትር አድርገው የሾሙበት ዕለት በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ ዕለት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ 12 ደቂቃ ገደማ የፈጀ ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ቅድሚያ  ሰጥተው ያነሱት ጉዳይ ባለፈው መስከረም አጋማሽ ወር በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ውጊያ ነው። በሰሜን ወሎ፣ በዋግ እና በአፋር ግንባሮች የተካሄደውን ውጊያ “ጦርነት” ሲሉ የጠሩት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፤ ጦርነቱን “የከፈተው” ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሆኑን ተናግረዋል።

ህወሓትን “በመላክ” ጦርነት እንዲከፍት ያደረጉት፤ “ከግብጽ እስከ ካርቱም እና አስመራ የተቀናጀው ጽምጾ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ጠላቶቻችን” ሲሉ የጠሯቸው ሀገራት፤ ለህወሓት በኤርትራ በሚገኘው የምጽዋ ወደብ በኩል የጦር መሳሪያ “አስተላልፈዋል” ሲሉም ከስሰዋል።

የተላለፈው የመሳሪያ መጠን “የአንድ መጠነኛ አገር የመከላከያ ትጥቅ ሊሆን የሚችል” እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፤ ይህም በመከላከያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል። የመከላከያ ሰራዊት “ከተቆጣጠራቸው” ከእነዚህ መሳሪያዎች መካከል የተወሰኑትን ባለፉት ሳምንታት ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ የውጭ ሀገር ወታደራዊ አታሼዎች እና ዲፕሎማቶች ማሳየቱ ይታወሳል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዛሬው ንግግራቸው “የውጭ ጠላት” እና “ሀገር አፍራሽ ባንዳዎች” ሲሉ የጠሯቸውን አካላት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለ119 ዓመታት፣ በአራት መንግስታት ስር ሆኖ ሲዋጋ መቆየቱን አስታውሰዋል። አምስተኛው መንግስት ባለበት በአሁኑ የስልጣን ዘመን ላይ፤ “ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲወጋን እና ሲያዋጋን የኖረ ጠላት፤ በአማራ፣ በኦሮሞ እና በትግራይ ህልውና ውስጥ ተደብቆ እየወጋን ይገኛል” ሲሉም ተደምጠዋል። 

“ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲወጋን እና ሲያዋጋን የኖረ ጠላት፤ በአማራ፣ በኦሮሞ እና በትግራይ ህልውና ውስጥ ተደብቆ እየወጋን ይገኛል”

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የእዚህን ጠላት ማንነት ከመግለጽ ቢቆጠቡም፤ “የኢትዮጵያ ማንሰራራት የህልውና አደጋ ያመጣብኛል” የሚል መሆኑን ግን በንግግራቸው ጠቁመዋል። “ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት እና ህዝቦች ጋር በወንድማማችነት እና በመልካም ጉርብትና ለመኖር ጽኑ ፍላጎት ያላት ቢሆንም፤ ‘በጥባጭ ካለ ማን ንጹህ ውሃ ይጠጣል’ ሆኖብናል” ሲሉም አክለዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህንን አስከትሎ ያነሱት የአባይ ውሃ እና የቀይ ባህር ጉዳይን ነው። “የአባይ ውሃ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋ ነው። ቀይ ባህር እኛ ኢትዮጵያውያን እንድንገለገልበት ፈጣሪ ያበጃጀው ባህር ነው” ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፤ ሁለቱም ውሃዎች “ለቀጠናው የሚበቁ” ቢሆንም “ብቻውን ሊጠቀልል የሚፈልግ” አካል እንዳለ ጠቁመዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “ገብጋባ” ሲሉ የወረፉትን ይህን አካል “እየታገልን ነው” ሲሉም ለበዓሉ ታዳሚያን ተናግረዋል። በአባይ ውሃ እና በቀይ ባህር የሚገኘውን “የኢትዮጵያን ጥቅም”፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና መከላከያ ሰራዊት “ከማስከበር ውጪ አማራጭ የላቸውም” ሲሉም በዛሬው ንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]

We are hiring!