የህወሓት ጽህፈት ቤት ወደ ትግራይ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ተቀየረ

የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል ያቋቋመው የባለአደራ አስተዳደር በዚህ ሳምንት ወደ ስራ ገብቷል። ከባለአደራ አስተዳደሩ ዋና አስፈጻሚዎች አንዱ የሆኑት አቶ ረዳኢ ሃለፎም በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር መመሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል።

“ለስራ መግባት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ‘ምንድነው ያለው? ምንድነው የሌለው?’ የሚሉ ጥናቶች ሲከናወኑ ነው የቆዩት። Almost ተጠናቅቀዋል፤ አሁን ወደ ስራ እንገባለን” ሲሉ አቶ ረዳኢ ተናግረዋል። “በየትኛውም አካባቢ ያላችሁ የክልሉ መንግስት ሰራተኞች፤ ወደ የስራ ቦታችሁ ሪፖርት አድርጋችሁ ስራችሁን መጀመር አለባችሁ” ሲሉም አሳስበዋል።

ስራቸውን ለሚጀምሩ ሰራተኞች “በቀናት ውስጥ ሁሉም ነገር ተሟልቶ ቢያንስ ደመወዝ መክፈል የምንጀምር ይሆናል” ሲሉም በባለአደራ አስተዳደሩ የፖለቲካ እና ህዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ረዳኢ አክለዋል። በመግለጫቸው ማግስት ከዚህ ቀደም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በጽህፈት ቤትነት ይገለገልበት የነበረውን ህንጻ ወደ ትግራይ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የመቀየር ስራ ሲከናወን ውሏል።

በባለአደራ አስተዳደሩ የጸጥታ እና ሰላም ዋና አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ብርጋዴየር ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ናቸው። “ወዲ አንጥሩ” በሚል ስማቸው ይበልጥኑ የሚታወቁት ብርጋዴየር ጄነራል ገብረእግዚአብሔር፤ ራሱን “የትግራይ ሰላም ኃይል” ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ሲመሩ የቆዩ ናቸው።

ብርጋዴየር ጄነራል ገብረእግዚአብሔር በበላይነት ይመሩታል ተብሎ የሚጠበቀው የትግራይ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የተረከበው የህወሓት ጽህፈት ቤት፤ ከዚህ ቀደምም እንዳሁኑ ለውጥ ተደርጎበት ያውቃል። የፌደራል መንግስት በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በህዳር 2013 ዓ.ም. ባቋቋመበት ወቅት፤ ጽህፈት ቤቱ ወደ ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤትን ተቀይሮ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

We are hiring!