በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን፤ በየትኛውም ቦታ ከአራት ሰዎች በላይ “እንዳይሰበሰቡ” ትዕዛዝ ተላለፈ

በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ “ከአራት ሰዎች በላይ እንዳይሰበሰቡ የሚከለክል” ትዕዛዝ ተላለፈ። በዞኑ በማታ የሚደረጉ የሰዎች እና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚከለክል የሰዓት እላፊ ገደብም ተጥሏል። 

ክልከላውን ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 8፤ 2019 ዓ.ም የጣለው፤ የሰሜን ምዕራብ ዞን ኮማንድ ፖስት ግብረ ኃይል ነው። በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ስር በሚገኘው የትግራይ ቴሌቪዥን በኩል የተሰራጨው የዛሬው የኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ አምስት ክልከላዎችን ይዟል። 

የሶስት ግለሰቦች ፊርማ እና ማህተም ያረፈበት ይህ ትዕዛዝ፤ በሰሜን ምዕራብ ዞን “ሰላም እና ጸጥታ ለማስፈን”፣ ለአካባቢው ህዝብ “ስርዓት ያለው ዕፎይታ እና ሰላም ለማምጣት” በማለም የተላለፈ መሆኑ በተሰራጨው ሰነድ ላይ ተመልክቷል። ትዕዛዙ የዞኑን “የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም” በማሰብ የወጣ እንደሆነም በዚሁ ሰነድ ላይ በተጨማሪነት ሰፍሯል። 

የሰሜን ምዕራብ ዞን በትግራይ ክልል ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ የሆነችውን ሽረ የሚያካትት ነው። የሽረ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ ትዕዛዝ መሰረት፤ ከማታ 12 ሰዓት ጀምሮ የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም። ለ24 ሰዓት እንዲንቀሳቀሱ ከተፈቀደላቸው አምቡላንሶች ውጪ ያሉ ተሽከርካሪዎችም፤ ከተጠቀሰው ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ኮማንድ ፖስቱ አስታውቋል።

ይኸው የኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ፤ ከመሀል አገር የሚመጡ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የመድኃኒት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGO) ከባድ ተሽከርካሪዎች “በተፈቀደላቸው አሰራር ብቻ እንዲንቀሳቀሱ” ውሳኔ ያሳለፈ ሆኗል። ከተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በዞኑ ነዋሪዎች ላይ ገደብ የጣለው ኮማንድ ፖስቱ፤ የሰዎች እንቅስቃሴ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ እንዲቆም ወስኗል።

ኮማንድ ፖስቱ በዚሁ ትዕዛዙ “በማንኛውም ጊዜ እና በማንኛውም ቦታ ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብ፣ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ መሆኑ እናስታውቃለን” ሲልም አክሏል። ዛሬ የወጣው ትዕዛዝ፤ ከጦር መሳሪያ ጋር የተያያዘ ክልከላ እና ቀነ ገደብም ለዞኑ ነዋሪዎች እና ለጸጥታ አካላት አስተላልፏል። 

በህግ ያልተፈቀደላቸውን የጦር መሳሪያዎችን እና ስለታም ነገሮችን ይዘው በተገኙ ግለሰቦች ላይ “አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው” ያስጠነቀቀው ኮማንድ ፖስቱ፤ ይህ ትዕዛዝ በዞኑ በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም አስታውቋል። ኮማንድ ፖስቱ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን ያሉ የጸጥታ አካላት፤ በእጃቸው የሚገኝ “ማንኛውምን የጦር መሳሪያ” በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ “ጽህፈት ቤት” እስከ ቀጣዩ ሳምንት ሰኞ ህዳር 14፤ 2019 ዓ.ም. ድረስ በመሄድ እንዲያስመዘግቡ ቀነ ገደብ ሰጥቷል።

የጸጥታ አካላቱ በተሰጣቸው ቀነ ገደብ የጦር መሳሪያዎችን ካላስመዘገቡ፤ “ቀጥሎ የሚመጣው ተጠያቂነት ከባድ መሆኑ እናስታውቃለን” ሲልም ኮማንድ ፖስቱ አስጠንቅቋል። የመከላከያ ሰራዊት ከአንድ ሳምንት በፊት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ እና ቀነ ገደብ፤ ለመቐለ ከተማ ነዋሪዎች መተላለፉ ይታወሳል።

የከተማይቱ ነዋሪዎች “ህጋዊ ፍቃድ የሌለው” የጦር መሳሪያዎቻቸውን በሶስት ቀናት ውስጥ ለትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲያስረክቡ በወቅቱ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር። ከዚሁ ጋር በአንድ ላይ በተላለፈ መመሪያም፤ በመቐለ ከተማ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል። የሰዓት እላፊ ገደቡ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

በሰሜን ምዕራብ ዞን ተግባራዊ እንዲደረግ የተላለፈው ትዕዛዝ፤ ከተሽከርካሪዎች እና ከሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ በተጨማሪ በአካባቢው ባለው የወርቅ ማውጣት ስራ ላይም ክልከላ ጥሏል። በዚህም መሰረት ኮማንድ ፖስቱ የወርቅ ማውጣት ስራዎች በዞኑ “ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም” ወስኗል።  

በወርቅ ማውጣት ስራ የተሰማሩ ኤክስካቫተሮች እና ሌሎች ማሽነሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡም ኮማንድ ፖስት ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል። “ይህንን የኮማንድ ፖስቱን ትዕዛዝ የሚጥስ አካል፤ በህዝብም ሆነ በአስተዳደሩ ለሚመጣ ተጠያቂነት ራሱ ኃላፊነቱን የሚወስድ ይሆናል” ሲልም ኮማንድ ፖስቱ አሳስቧል።

የሰሜን ምዕራብ ዞን ኮማንድ ፖስት ሌላው ያስተላለፈው ክልከላ ቢንጎ የተሰኘውን የዕድል ጨዋታ የሚመለከት ነው። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ወጣቶች “ለሞራል እና ማህበራዊ ቀውስ እየዳረገ ነው” ያለውን ቢንጎ ጨዋታ፤ “ላልተወሰነ ጊዜ” እንዲቆም መወሰኑን አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

We are hiring!