የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ መስከረም 28፤ 2019 ባካሄደው ስብሰባ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን 23 የካቢኔ አባላት ሹመት አጽድቋል። ባለፈው ሰኞ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመቀጠል ቃለ መሃላ የፈጸሙት አብይ ዛሬ ስራ አስፈጻሚውን ሲያዋቅሩ፤ ከቀደመው መንግስታቸው የካቢኔ አባላት መካከል 9 ሹማምንት በስልጣናቸው ቀጥለዋል።
ሶስቱ ሚኒስትሮች ወደ ሌሎች መስሪያ ቤት ተዛውረው ሲሾሙ 11ዱ ሚኒስትሮች በቀደመው ካቢኔ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ናቸው። ተሿሚዎቹ በትምህርት ዝግጅት፣ “በመፈጸም እና የመከታተል ብቃት” በስነ ስርዓት፣ በስራ ልምድ የተመዘኑ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
አዳዲሶቹ ተሿሚዎች “ሙስና የሚጠየፉ፤ ሙስናን ለመከላከል ጥረት የሚያደርጉ” እንዲሆኑ ጥረት መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩዎቻቸውን ለምክር ቤቱ በስም እየጠቀሱ ከማቅረባቸው በፊት አብራርተዋል። መንግስታቸው አዘጋጅቶታል ያሉትን “እስከ 2050 ዓ.ም የሚዘልቅ የመደመር ግራንድ ስትራቴጂ” ሚኒስትሮቹ “በቅጡ የተረዱ በዚህ ግራንድ ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጡ አበይ ነጥቦችን ከነ ዝርዝር እሳቤያቸው የተገነዘቡ” እንደሆኑም ገልጸዋል።

“በተቻለ መጠን የብሔር ስብጥር የጾታ ስብጥር የእምነት ስብጥር ለመጠበቅ ጥረት” መደረጉን አብይ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል። በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ሹመታቸው ከጸደቀላቸው ሚኒስትሮች መካከል ዘጠኙ ሴቶች ናቸው።
ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት መካከል በዛሬው ሹመት ስማቸው በቅድሚያ የተነሳው አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ በያዙት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን እንዲቀጥሉ ተደርገዋል። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል የነበሩት አቶ ተመስገን፤ የቀድሞውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን በመተካት ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሸጋገሩት በጥር 2016 ዓ.ም. ነበር።
እንደ አቶ ተመስገን ሁሉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቁልፍ የሆኑትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴርን ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና አዲሱ አረጋ፤ በአዲሱ መንግስት ውስጥ ቦታቸውን አስከብረዋል። ከሁለት ዓመት በፊት ከፍትህ ሚኒስቴርነት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተዘዋወሩት ዶ/ር ጌዲዮን፤ “ወደፊት” “የአፍሪካን ጉዳይ አጉልቶ ሊያነሳ የሚችል ምርጥ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የመሆን ብቃት” እንዳላቸው አብይ ለምክር ቤቱ በዕጩነት ባቀረቧቸው ወቅት መስክረውላቸዋል።

የዶ/ር ጌዲዮን ባለቤት የሆኑት የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርአያ ስላሴ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በያዙት ስልጣን ከቀጠሉ ሹማምንት መካከል ናቸው። የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሃብታሙ ኢተፋ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴም እንዲሁ በያዙት ስልጣን ቀጥለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቢኔን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በቱሪዝም ሚኒስትር የተቀላቀሉት ሰላማዊት ካሳ፤ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴርን በኃላፊነት እንዲመሩ በድጋሚ ተሹመዋል። ሰላማዊት የተሾሙበት መስሪያ ቤት የባህል ሚኒስቴር እና የቱሪዝም ሚኒስቴር ተዋህደው የተፈጠረ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































