በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ሲጀመር ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ፋኖ በአማራ እና አፋር ክልሎች ጠልቀው በመግባት የጅቡቲን መስመር እንዲቆርጡ በኤርትራ መንግስት “ትዕዛዝ” ተሰጥቷቸው እንደነበር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። ውጊያው በአፋር ክልል ወደሚገኙ አካባቢዎች ሲዘልቅ “የኤርትራ ኃይል በተወሰነ ደረጃ” በከባድ መሳሪያ “ድጋፍ” እያደረገ፤ ለኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ ቁልፍ መተላለፊያ የሆነውን የጅቡቲ አውራ ጎዳና የመቁረጥ ስሌት እንደነበር አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
ላለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ውጊያውን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ባዘጋጁት የፖሊሲ የውይይት መድረክ ላይ ነው። “ህብረት ወይስ ክደት? ጸረ-ኢትዮጵያ ጥምረት ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 12፤ 2019 የተካሄደውን ውይይት በአብዛኛው የታደሙት፤ የመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው።
በመድረኩ ማብራሪያ ያቀረቡት አቶ ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ወደ ለየለት ፍጥጫ የከተተውን አዲስ ውጊያ በተመለከተ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በሚደረገው ግንኙነት የግንባር ሰው ናቸው። አቶ ጌታቸው ዛሬ አንድ ወር የደፈነውን ውጊያ በተመለከተ ማብራሪያ ከሰጧቸው ዲፕሎማቶች መካከል በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሺያ እና የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር ይገኙበታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካሪ በዚሁ ሚናቸው ትላንት ረቡዕ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጉዋንግ ኮንግ ተገናኝተው ተወያይተዋል። አቶ ጌታቸው በዚሁ ውይይታቸው፤ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ “ስለተፈጠሩ ሁኔታዎች” እና አዲስ ስለ ተቋቋመው የትግራይ ክልል የባለአደራ አስተዳደር ማብራሪያ መስጠታቸውን በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ግጭት በማቆም ስምምነት ለአራት ዓመታት ገደማ የተገታው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፤ የትግራይ ክልል ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ዳግም ሲያገረሽ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል። በውጊያው ምክንያት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤትን ትኩረት ጭምር የሳበ ነው።
አዲሱ ውጊያ የተጀመረው፤ ህወሓት እና የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የሚገኙበት “የኢትዮጵያ ህዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለህልውና” የሰባት አማጽያን ኃይሎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ መመስረቱ ይፋ በተደረገ በሁለተኛው ቀን ነበር። ትብብሩ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት “በማስወገድ”፤ “አካታች የሽግግር መንግስት” ለመመስረት ያለመ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
አቶ ጌታቸው በዛሬው ውይይት ላይ በ“ትብብር ለህልውና” የተሰባሰቡ አማጽያንን “የማስተባበር” ሂደት “ረዥም ጊዜ የወሰደ” እንደሆነ ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካሪ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ ትብብሩን በትግራይ እና በኤርትራ “የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት” ተደርጎ ይቀርብ ከነበረው “ጽምዶ” ጋር አንድ እና ያው አድርገውታል።
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጌታቸው፤ “ጽምዶ” በቀድሞ ፓርቲያቸው ላይ በኤርትራ “የተጫነ ነው” የሚል እምነት አላቸው። በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ሲጀመር ህወሓት እና ፋኖ በአማራ እና አፋር ክልሎች ጠልቀው በመግባት የጅቡቲን መስመር እንዲቆርጡ በኤርትራ መንግስት “ትዕዛዝ” ተሰጥቷቸው እንደነበርም የዛሬውን ውይይት ለታደሙ ተሰብሳቢዎች አስረድተዋል።
ውጊያው በአማራ ክልል በሰቆጣ፣ በቆቦ እና በሮቢት አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል በኤረብቲ አድርጎ ወደ አፍዴራ ሲዘልቅ፤ “የኤርትራ ኃይል በተወሰነ ደረጃ” በከባድ መሳሪያ “ድጋፍ” እያደረገ የጅቡቲ አውራ ጎዳናን የመቁረጥ ስሌት እንደነበር አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።

በአማራ እና አፋር ክልሎች በኩል ከሰሜን ወደ ደቡብ በሚደረገው ውጊያ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት “ሲደመርበት”፤ “መንግስት ይወድቃል፤ ቢያንስ ቢያንስ ለድርድር ይቀርባል” የሚል ስሌት አማጽያኑ እንደነበራቸውም አቶ ጌታቸው አክለዋል። ይሁንና በመንግስት በኩል “የተደረገው ዝግጅት እና እነሱ ያሰቡት ነገር የሚገናኝ አልነበረም” ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካሪ ተደምጠዋል።
በወሎ፣ ዋግ እና ሰሌን ውሃ አካባቢዎች በተደረጉ ውጊያዎች “ብዙ የትግራይ ሰራዊት አባላት ተገድለዋል” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በ2013 ዓ.ም. በተደረገ ውጊያ አካባቢውን ለመቆጣጠር “የወሰደው ጊዜ እና የተጠየቀው መስዋዕትነት” በጣም አነስተኛ እንደነበር መለስ ብለው አስታውሰዋል። ከዚህ በኋላ የትግራይ ኃይሎች “ጸረ ማጥቃት” ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችልም ተናግረዋል።
“ጦርነቱ አብቅቷል” የሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ፤ “ከሶሻል ሚዲያ ውጪ የተደራጀ resistance አሁን ትግራይ ውስጥ የለም” ሲሉም ተደምጠዋል። “ሁሉም ከተሞች ካስያዝክ በኋላ ‘ገጠር ውስጥ ነው ያለሁት’ ትላለህ። ሁሉም ገጠሮች እየታሰሱ ነው” ሲሉም አክለዋል።

መከላከያ ሰራዊት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ከኤርትራ ድንበር በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ “አዲ ፍታው” የተባለች ቦታ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ግጭት ቢፈጠር “የኤርትራ ምሽግ የመሰበር እድሉ ሰፊ ነው። ምሽጉ ከተሰበረ በኋላ አስመራ ለመግባት የሚወስድ በጣም አጭር ጊዜ ነው” ብለዋል።
የኤርትራ መንግስት አለበት ያሉትን “strategic depth እጥረት” ለማካካስ፤ “ጦርነቱን ከራሱ ድንበር አርቆ” ኢትዮጵያን “የማተራመስ ስልት” እንደሚከተል አቶ ጌታቸው በዛሬው ውይይት ላይ በተደጋጋሚ አንስተዋል። በትግራይ ክልል ውጊያ ሲደረግ “የኤርትራ መንግስት አጉላዕ ላይ ለማስቆም ጥረት” አድርጎ እንደነበር አቶ ጌታቸው ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኤርትራ ወታደሮች ተራራማ በሆኑት ዕዳጋ ሓሙስ እና ዕዳጋ እሮብ አካባቢዎች በመመሸግ መከላከል ቢፈልጉም፤ በመከላከያ ሰራዊት መመታት ሲጀምሩ ከግንቦት 1990 ዓ.ም. ጦርነት በፊት ወደነበረ ምሽጋቸው እንደተመለሱ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል። የኤርትራ ወታደሮች “ባድመንም ጭምር” መልቀቃቸውን የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

የኤርትራ ወታደሮች በሶስት የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ለተመድ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት መስከረም 28፤ 2019 በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀው ነበር። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ሰዎች” “ምን ልታደርጉ ነው?” ብለው እንደሚጠይቋቸው ለዛሬው ውይይት ተሳታፊዎች የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ “እነዚህን ሰዎች ለማስቆም እየተከታተልክ ብትገባ ዓለም አቀፍ ህግም አይከለክልህም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት “ሊያርቁ ያሰቡት ግጭት” በትብብር ለህልውና “መፍረስ ምክንያት አፍንጫቸው ስር ደርሷል” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ያላቸው “ምርጫ” ሁለት እንደሆነ ገልጸዋል። አንደኛው ምርጫ ኢትዮጵያን “ግርግር ውስጥ ለማስገባት ለሚፈልጉ ኃይሎች የሚሰጠውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በአደባባይ እና በተግባር ማቆም” የሚል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ያለው አማራጭ “ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትና ያስፈልገኛል፤ በሁሉም ጉዳዮች ላይ በውይይት ላይ የተመሰረተ ሰላም መፍጠር እፈልጋለሁ” የሚል “commitment መግባት” እንደሆነ አስገንዝበዋል። ይህ ካልሆነ የሚፈጠረውን ለመግለጽ አቶ ጌታቸው የተጠቀሙት፤ “ኬኩን በልተኸውም፣ አቆይተኸውም አይሆንም” የሚለውን የፈረንጆች ተረት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































