ኢትዮጵያ በዘንድሮው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ 6.76 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህ የገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ2.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ እድገት ያለው መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 23፤ 2018 የስምንት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው። የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ በዚሁ ስብሰባ ላይ፤ የዘንድሮው የስምንት ወራት ገቢ በኢትዮጵያ ታሪክ “ተገኝቶ የማይታወቅ” መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ፤ የስምንት ወራቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በ2018 ይደረስበታል ተብሎ ከታቀደው የሶስት ዓመቱ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ የሆነበትን ምክንያት ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትል የሚያደርግባቸው የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ሰብሎች እና የእንስሳት መኖ የወጪ ንግድ አፈጻጸምም ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለበትን ምክንያት እንዲገለጽም ቋሚ ኮሚቴው በተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቧል።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ባለፉት ስምንት ወራት የተመዘገበው የወጪ ንግድ የገቢ መጠን፤ ከሶስት ዓመት ዕቅድ አንጻር ካልሆነ በስተቀር “ዝቅተኛ ሊባል የሚችል አይደለም” ሲሉ ተሟግተዋል። “ከለውጡ በኋላ” በነበሩት ጊዜያት በየሁለት ዓመቱ ይገኝ የነበረውን የወጪ ንግድ ገቢ በስምንት ወራት ውስጥ ማሳካት የተቻለበት መሆኑንም ለቋሚ ኮሚቴው አባላቱ በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ሰብሎችን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ደግሞ በእነዚህ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የፍላጎት መቀዛቀዝ እንዲሁም የዋጋ መውረድ መታየቱን ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት በቅባት እህሎች የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከእቅድ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ዶ/ር ካሳሁን ተናግረዋል። ሆኖም ሀገሪቱ ውጭ የላከችው የምርት መጠን በእቅድ ከተቀመጠው በላይ መሆኑን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































