የኢትዮጵያ እና የሱዳን ውጥረት ወደ ወታደራዊ እና ቀጠናዊ ግጭት እንዳያመራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በሁለት ልዩ ልዑካን ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ። በሁለቱ ጎረቤት አገሮች መካከል የበረታው ውጥረት በቅርብ ቀናት ውስጥ “አስከፊ ደረጃ” ላይ እንደደረሰ የገለጹት የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሀን ሃቅ፤ ሁኔታው “የበለጠ እንዳይባባስ እንፈልጋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ ወደ 744 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚረዝም ድንበር በሚጋሩት በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተከሰተው ውጥረት በተለይ ባለፈው አንድ ወር ገደማ እየተባባሰ ሄዷል። በውጥረቱ ምክንያት የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች፤ በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በተመድ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እስከመካሰስ ደርሰው ነበር።
ሁለቱ ሀገራት በጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት በአሶሳ እና በገዳሪፍ የነበሩ ቆንስላዎችን በመዝጋት፤ አንዳቸው የሌላውን ዲፕሎማቶች እንዳባረሩ አሶሴትድ ፕሬስ እና ሮይተርስ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በአብደል ፋታህ አል ቡርሃን የሚታዘዘው የሱዳን ጦር፤ “ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድጋፍ ያደርጋል” ሲሉ ይወነጅላሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት ከተመድ ዋና ጸሀፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጉዋንግ ኮንግ በተገናኙበት ወቅትም ይኸው ጉዳይ መነሳቱ ተገልጿል። በዚሁ ውይይት ወቅት፤ አቶ ጌታቸው “አፍራሽ” ላሏቸው ኃይሎች አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን የጦር መሳሪያ “በማስታጠቅ፣ በማቅረብና በማስተባበር” ስለሚያደርጉት ድጋፍ ለአምባሳደሩ ማብራሪያ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ያለው “ውጥረቱ የበለጠ እንዳይባባስ” ኢትዮጵያ “ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ” እንደምትፈልግ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ይህ እንዲሆን ግን አል ቡርሃን እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ታጣቂዎችን ከመደገፍ እና ከማስታጠቅ መቆጠብ አለባቸው” የሚል አቋም እንዳላት ለልዩ ልዑኩ ማስረዳታቸውን በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
በሱዳን ጦር የሚመራው ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት በበኩሉ፤ በሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ለሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል “ኢትዮጵያ ድጋፍ ታደርጋለች” በማለት ይከስሳል። በአብደል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው ይኸው ምክር ቤት፤ ከኢትዮጵያ ግዛት በሚወነጨፉ ድሮኖች “በሰላማዊ ሰዎች እና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም” ባለፈው ወር ይፋዊ ውንጀላ አቅርቧል።
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረውን ውንጀላ “የሚያሳዩ ናቸው” ያላቸውን ማስረጃዎች፤ ለተመድ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እና ለአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት ማቅረቡንም አስታውቋል። የተመድ ዋና ጸሀፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋራሃን ሃቅ ትላንት ሰኞ ህዳር 7፤ 2019 በሰጡት ዕለታዊ መግለጫ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት “በእርግጥም አሳስቦናል” ብለዋል።
ለውጥረቱ መፍትሔ ለማበጀትም፤ የመንግስታቱ ድርጅት ለሱዳን እና ለአፍሪካ ቀንድ በመደባቸው ልዩ ልዑካን አማካኝነት ግፊት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ፋራሃን ሃቅ ገልጸዋል። የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የሱዳን ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ በቅርቡ በአቡዳቢ ባደረጉት ጉብኝት፤ ከሱዳን እና ቀጠናዊ አገናኞች እንዲሁም ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ምክትል ቃል አቃባዩ አስረድተዋል።
ፊንላንዳዊው ዲፕሎማት ሐቪስቶ ውይይታቸውን ለመቀጠል በመጪዎቹ ሳምንታት ወደ ሱዳን ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ፋራህን ሃቅ አመልክተዋል። ምክትል ቃል አቃባዩ በትላንቱ መግለጫቸው፤ ሁለቱ ልዩ ልዑካንም ሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት ኃላፊዎች በሱዳን ግጭት ውስጥ “የኢትዮጵያ ተሳትፎ” ስላስከተለው ችግር “ግንዛቤ አላቸው” ሲሉ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































