በትግራይ ክልል “ውጊያ የተሳተፉ” ግለሰቦች በአካባቢ ምርጫ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ደንብ ጸደቀ

በትግራይ ክልል የተቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር “በባለፈው የህገወጡ ቡድን ውጊያ” እንዲሁም “ጸረ ህዝብ” ባላቸው ዘመቻዎች “የተሳተፉ” ግለሰቦች በምርጫ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ደንብ አጸደቀ። ደንቡ በክልሉ በተለያዩ እርከኖች የሚገኙ አስተዳደሮችን ለመምራት ዕጩ ሆነው የሚቀርቡ ግለሰቦች፤ “ከፖለቲካዊ ውግንና ነጻ መሆን” እንደሚገባቸውም ደንግጓል።

የባለአደራ አስተዳደሩ ካውንስል የወቅቱ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ አሰፋ አብርሃ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደንብ፤ “የትግራይ ክልል የአስተዳደር አካላት መዋቅርን ለመወሰን” የወጣ ነው። በሶስት ክፍሎች የተከፋፈለው ይህ ደንብ፤ የምርጫ፣ የምርጫ ሂደት እና ሹመትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው። 

“ጠቅላላ ድንጋጌዎችን” የያዘው የመጀመሪያው የደንቡ ክፍል፤ የቃላት ትርጓሜዎች እና የተፈጻሚነት ወሰን የተካተቱበት ነው። በዚህ የሰነዱ ክፍል ላይ ደንቡ ተፈጻሚ የሚሆነው፤ በትግራይ ክልል አስተዳደር መዋቅር ውስጥ “በህዝብ በቀጥታ በሚካሄድ ምርጫ፣ የምርጫ ሂደት፣ የሹመት አሰጣጥ እና ማንሳት እንዲሁም ተጠሪነት ላይ” እንደሆነ ሰፍሯል።

ምርጫዎች የሚደረጉት ለከተማ አስተዳደር፣ ለወረዳ እና ክፍለ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ዝቅተኛው የአስተዳደር እርከን ለሆነው ለጣቢያ አስተዳደር እንደሆነ በደንቡ ላይ ሰፍሯል። እነዚህን ምርጫዎች “የሚያስተናግዱ አስተባባሪዎችን መልምሎ፣ አደራጅቶ እና አሰልጥኖ ወደ ወረዳ፣ ከተማ አስተዳደር ወይም ክፍለ ከተማ የመላክ” ስልጣን በደንቡ የተሰጠው ለባለአስተዳደሩ ካውንስል ነው። 

ካውንስሉ ባለፈው ጥቅምት 6፤ 2019 በፌደራል መንግስት የተሾሙ አራት ዋና ስራ አስፈጻሚዎች አባል የሆኑበት ነው። የተለያዩ ዘርፎችን የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸው አራቱ ተሿሚዎች፤ አቶ አሰፋ አብርሃ፣ ብርጋዴር ጀነራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥሩ)፣ አቶ ረዳኢ ሓለፎም እና ዶ/ር ቴዎድሮስ አረጋይ ናቸው።

የባለአደራ አስተዳደሩ ካውንስልን በሰብሳቢነት የመምራት ኃላፊነት በየ45 ቀኑ በየተራ የሚደርሳቸው ዋና ስራ አስፈጻሚዎቹ፤ በፌደራል መንግስት የተሰጣቸው የስራ ጊዜ ስድስት ወራት ብቻ ነው። ባለአደራ አስተዳደሩ በዚህ ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል “ሰላማዊ እና አካታች” ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ስራ ከጀመረ 10 ቀናት ያለፉት የባለአደራ አስተዳደሩ፤ የምርጫ፣ የምርጫ ሂደት እና ሹመትን የሚወሰነውን ደንብ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። ካለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 21፤ 2019 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በተገለጸው በዚህ ደንብ ላይ፤ የዞን አስተዳደር ሹመት በትግራይ ባለአደራ አስተዳደር ካውንስል በቀጥታ እንደሚሰጥ ሰፍሯል።

በዚሁ ደንብ ላይ የከተማ፣ የወረዳ፣ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ጣቢያ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለመሆን በዕጩነት የሚቀርቡ ተመራጮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ 12 መስፈርቶች ተዘርዝረዋል። ከመስፈርቶቹ መካከል “ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ፣ የክልሉን የስራ ቋንቋ የሚችል፣ በዕጩነት የቀረበበት አካባቢ ተወላጅ ወይም ነዋሪ የሆነ” የሚለው ይገኝበታል። 

ተመራጮች ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 45 መሆን እንዳለበትም ገደብ የሚያስቀምጠው ደንቡ፤ በዕጩነት የሚቀርቡ ግለሰቦች የትምህርት ደረጃንም በመስፈርትነት አካትቷል። ለከተማ፣ ክፍለከተማ እና ወረዳ አስተዳደሮች በዕጩነት የሚቀርቡ ተመራጮች የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖራቸው እንደሚገባ፤ ለጣቢያ አስተዳዳሪነት የሚታጩ ደግሞ ቢያንስ 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ መሆን እንዳለባቸው ደንቡ ያስገድዳል።

ዕጩዎች “ከፖለቲካዊ ውግን እና ነጻ መሆን እንዳለባቸው” ግዴታ የሚያስቀምጠው ይኸው ደንብ፤ ተመራጮቹ “በባለፈው የህገወጡ ቡድን ውጊያም ይሁን በሌላ ጸረ ህዝብ ዘመቻ ያልተሳተፉ” መሆን እንደሚገባቸውም ደንግጓል። ይሁንና ደንቡ “የባለፈው ውጊያ“ ብሎ የጠቀሰው፤ በቅርብ ጊዜ የነበረውን ይሁንአሊያም ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም. የተካሄደውን በግልጽ አላስቀመጠም።

በደንቡ “ጸረ ህዝብ ዘመቻ“ በሚል የተቀመጠው ገለጻም በደፈናው የቀረበ ነው። ይኸው ደንብ በተጨማሪነት፤ ዕጩ ተመራጮች የኢፌዲሪ ህገ መንግስት እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን “የሚቀበሉ” መሆን እንደሚጠብቅባቸውም በመስፈርትነት አካትቷል።

“የምርጫ፣ የምርጫ ሂደት እና ሹመትን የሚወስነው” ደንብ፤ ለባለአደራ አስተዳደር ካውንስሉ ምርጫውን በተመለከተ “መመሪያ” የማውጣት ወይም “ውሳኔ” የማስተላለፍ ስልጣንም ሰጥቷል። ካውንስሉ ይህንን የሚያደርገው “ምርጫ ማካሄድ በማይቻልበት አጋጣሚ” አሊያም ምርጫው “አግባብነት የለውም ወይም ተጭበርብሯል ብሎ ካመነ” እንደሆነ በደንቡ ላይ ተብራርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

We are hiring!