የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ ለምርጫ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እና የአፋር ህዝብ ፓርቲ ለመጪው ምርጫ በጋራ ለመስራት ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 3 ተፈራረሙ። በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ሙሳ አደም እና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም ናቸው።

ሁለቱ ፓርቲዎች አስቀድመው በደረሱበት መግባባት መሰረት ሀገር አቀፍ ፓርቲ የሆነው የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ድምጽ ላለመከፋፈል በአፋር ክልል ዕጩዎቹን አለማቅረቡን አስታውቀዋል። ሀገር አቀፍ ፓርቲው በአፋር ክልል የሚገኙ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ  የአፋር ህዝብ ፓርቲን ዕጩዎች እንደሚመርጡ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ተጣማሪው የአፋር ህዝብ ፓርቲም ከክልሉ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ተመሳሳዩን እንደሚያደርግ አስታውቋል። 

የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ሙሳ አደም “የተፈራርምነው ስምምነት በተለይ ከዚህ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የአፋር ህዝብ እና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በጋራ ሁለቱም ማሸነፍ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተደረገ ስምምነት ነው” ብለዋል። 

ሁለቱ ፓርቲዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ውይይቶች ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት ዶ/ር አብዱልቃድር፤ የዛሬውን ስምምነት ለፓርቲያቸው “አንድ ትልቅ ዕድል” ተናግረዋል። ስምምነቱንም “ታሪካዊ” ሲሉ ጠርተውታል። 

“ነእፓ ትኩረት ከሚሰጣቸው የማህብረሰብ ክፍሎች አንዱ የሆነው የአርብቶ አደር ማህበረሰብን የልማት፣ የዲሞክራሲና የሰላም ጥያቄ ለመፍታት ከፓርቲው ጋር ብዙ አይነት ድርድሮች ስናደርግ ቆይተናል። በስምምነቱ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው አንዱና ቁልፍ የነበረው የምርጫ ጉዳይ ነበር። ይሄ ስምምነት መፈረም የነበረበት የዕጩዎች ምዝገባ ከመደረጉ በፊት ነበር። በተለያዩ ቴክኒካል እና ሌሎች ምክንያቶች ወደ ዛሬ ዘግይቷል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)