በሃሚድ አወል
ከአምስት ቀናት በኋላ በሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ከትግራይ ክልል ውጪ ለ64 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ እንደማይሰጥ ታወቀ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ለ64ቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ድምጽ የሚሰጠው ጷጉሜ 1፤ 2013 ነው።
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጠቃላይ የመቀመጫ ብዛት 547 ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 38 ያህሉ በትግራይ ክልል ምርጫ የማይካሄድ በመሆኑ ከውድድር ውጭ መሆናቸው ይታወሳል። ሰኔ 14 ለሚካሄደው ምርጫ ቀደም ሲል ለውድድር ቀርበው የነበሩት 509 የፓርላማ መቀመጫዎች ነበሩ። ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባሰራጨው መረጃ መሰረት፤ በመጪው ሰኞ ምርጫ የሚከናወንባቸው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ብዛት 445 መሆኑ ታውቋል።

ስልሳ አራት የምርጫ ክልሎች ከሰኔ 14ቱ ምርጫ ውጪ ከተደረጉባቸው ምክንያቶች መካከል፤ በጸጥታ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት የመራጮች ምዝገባ አለመከናወን አንዱ መሆኑን ምርጫ ቦርድ ገልጿል። የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ላይ የተፈጠረ እክል እንዲሁም ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያሉት የፍርድ ቤት ሙግቶችም በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል።
እንደ ቦርዱ መረጃ ከሆነ ከስልሳ አራቱ የፓርላማ መቀመጫዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑቱ የሚወክሉት የሶማሌ እና የደቡብ ክልሎችን ነው። ሰኔ 14 ሙሉ ለመሉ ምርጫ የማይካሄድበት የሶማሌ ክልል በ23 የፓርላማ መቀመጫዎች ዝርዝሩን የሚመራ ሲሆን፤ ደቡብ ክልል በ16 መቀመጫዎች ይከተላል።

የአማራ ክልል መራጮች ለ10 የፓርላማ መቀመጫዎች ሰኔ 14 ድምጽ የማይሰጡ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 7 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ለምርጫ አይቀርቡም። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4 የፓርላማ መቀመጫዎች በሰኔ 14ቱ ምርጫ አልተካተቱም።
እንደ ሶማሌ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ምርጫ በማካይሄድበት ሐረሪ ክልል፤ 2 የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ላይ ሰኞ ዕለት ድምጽ አይሰጥም። በአፋር ክልልም 2 የፓርላማ መቀመጫዎች ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)