አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በመሆን በድጋሚ ተመረጡ

በተስፋለም ወልደየስ

የኦሮሚያ ክልልን ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የመሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ክልሉን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በድጋሚ ተመረጡ። አቶ ሽመልስ ለክልሉ መሪነት የተመረጡት ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 15፤ 2014 በአዳማ በተካሄደ የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ ነው። 

በዛሬው ጉባኤ፤ የኦሮሚያ ክልልን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለማስተዳደር ከአቶ ሽመልስ ውጭ ሌላ ተቀናቃኝ ዕጩ ለምክር ቤቱ ያልቀረበ ሲሆን የድምጽ መስጠት ስነ ስርዓትም አልተከናወነም። የክልሉ ገዢ ፓርቲ ቃል አቃባይ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በዚህ አካሄድ ላይ ጥያቄ ቢያነሱም፤ በአዲሷ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ በኩል ተቀባይነት አላገኘም።

ከዚህ በኋላ አቶ ሽመልስ ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን፤ ለክልሉ ምክር ቤት አባላትም ንግግር አድርገዋል። ይህንን ተከትሎም 32 አባላት ያሉበትን ካቢኔያቸውን ተሿሚዎች ዝርዝር ለጨፌ ኦሮሚያ አቅርበዋል። በርካታ አዳዲስ ፊቶችን ወደፊት ያመጣውን የዛሬውን የካቢኔ አባላት ሹመት፤ 12 የምክር ቤት አባላት የተቃወሙት ሲሆን አስራ ሶስት አባላት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።  

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት፤ አቶ አወሉ አብዲ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል

በዛሬው ሹመት ከፍተኛውን ቦታ ያገኙት  ቀደም ሲል የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ አወሉ አብዲ ናቸው። አቶ አወሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትነትን ስልጣን ከጫልቱ ሳኒ ተረክበዋል። 

አቶ አወሉ፤ ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣታቸው አስቀድሞ ላለፈው አንድ ዓመት የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚን ሲመሩ ቆይተዋል። የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ማሰልጠኛ የሆነው ይህ ተቋም፤ ስያሜውን ወደ አፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የቀየረው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር።

በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ አምስት ኃላፊዎች በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ሹመት አግኝተዋል

በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ አምስት ኃላፊዎች በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ሹመት አግኝተዋል። በሹመቱ ከተካተቱት ውስጥ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ማዕረግ የሰሩት ዶ/ር ግርማ አመንቴ እና አቶ አዲሱ አረጋ ይገኙበታል። ዶ/ር ግርማ የክልሉ ሀብት እና ንብረት ክላስተር አስተባባሪ በመሆን ሲሾሙ፤ አቶ አዲሱ ደግሞ የከተማ ልማት  ክላስተር አስተባባሪ ሆነዋል። 

የኦነግ አንደኛውን ክንፍን ሲመሩ የቆዩት አራርሶ ቢቂላ፤ ዛሬ በተመሰረተው አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ካቤኒ ውስጥ ሹመት አግኝተዋል

በዛሬው ሹመት፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ አራርሶ ቢቂላ የቢሮ ኃላፊነት ስልጣን ማግኘታቸው ያልተጠበቀ ሆኗል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንደኛውን ክንፍን ሲመሩ የቆዩት አቶ አራርሶ፤ የክልሉን የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኃላፊነት እንዲመሩ ነው የተሾሙት። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)