መንግስት ለመጪው ምርጫ “ሰላማዊ የውድድር ሜዳ እንዲፈጥር” አራት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ

በቤተልሔም ሠለሞን

በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ አንድ ዓመት ከመቅረቱ አኳያ፤ ገዢው ፓርቲ “እውነተኛ” እና “ሁሉን አካታች” የሆነ ድርድር “በአስቸኳይ” በማድረግ እና በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ቀውሶችን በመፍታት፣ “ሰላማዊ የውድድር ሜዳ እንዲፈጥር” አራት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ። ፓርቲዎቹ “ለሰላማዊ ትግል ውጤታማነት” እገዛ ለማድረግ፤ መንግስት “የፖለቲካ እስረኞችን” እንዲፈታም ጠይቀዋል።

ዛሬ ሰኞ ግንቦት 4፤ 2017 በጋራ ባወጡት መግለጫ ጥሪ፣ ጥያቄ እና ማሳሰቢያቸውን ያቀረቡት፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ናቸው። በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠው የአራቱ ፓርቲዎች የዛሬ መግለጫ ትኩረቱን ያደረገው፤ በ2018 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ሰባተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ነው። 

“ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ካለችበት የጦርነት አዙሪት ለመውጣት እና የህዝብ ጭቆና፣ አፈና፣ ሰቆቃና እልቂትን ማስቆም የሚቻለው፤ ከማጭበርበር የጸዳ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ምርጫ በማካሄድ ብቻ መሆኑን እኛ በሰላማዊ መንገድ የምንታገል የትብብር ፓርቲዎች በጽኑ እናምናለን” ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል። እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ ምርጫ፤ በተፈጥሮው “ሰላማዊ የመከወኛ ሜዳ የሚሻ” መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከምርጫው ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው ጉዳዮች “ከዕለት ወደ ዕለት መሻሻል ማሳየት” ይገባቸው እንደነበር የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታዩ እውነቶች ከዚህ የተቃረኑ መሆናቸውን አመልክተዋል። ፓርቲዎች ለዚህ አባባላቸው በማሳያነት ያነሱትል፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች “የተፋፋመ ነው” ያሉትን ጦርነት እና የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ ነው።

ፓርቲዎቹ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት በተደነገገው መሰረት አንድ ዓመት ብቻ በቀረው ሀገራዊ ምርጫ፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለሲቪክ ተቋማት መደረግ የሚገባውን በመግለጫቸው ዘርዝረዋል። በምርጫ ሂደት ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ “እንደልባቸው ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተገናኝተው ውይይቶችን ለማድረግ ግብታዊ እርምጃዎች፣ ወከባዎች እና ክልከላዎች ሊነሱ ይገባል” ሲሉም በመግለጫቸው አሳስበዋል።

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን “የአንድ ስርዓት አወዳሽነትን” በማስወገድ “ወደ ፍትሃዊነት መምጣት አለባቸው” ሲሉ ፓርቲዎቹ አቋማቸውን አስታውቀዋል። ፓርቲዎቹ “ገለልተኛ” በሚባሉ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተጥሏል ያሉት “የማስፈራሪያ ቀንበር” “ሊቀልላቸው ይገባል” ብለዋል። 

እንደ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ የመንቀሳቀሳ ምህዳሩ ለሰብዓዊ መብት፣ የሲቪክ እና ዴሞክራሲ ተቋማት “የበለጠ ገለልተኛ” እና “ይበልጥ አሳታፊ” ሊሆንላቸው እንደሚገባ ፓርቲዎቹ አሳስበዋል። የመጪውን ምርጫ ሂደት በርከት ያሉ ታዛቢዎች እንዲከታተሉ፤ “መደላደል ሊፈጠር” እንደሚገባም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል።

አራቱ ፓርቲዎቹ እነዚህን ጉዳዮች በማጤን ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት “በአዲስ መልክ ለመቀየር” ሂደቱ መጀመሩ እንዳሳሰባቸውም አመልክተዋል። የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ እና ሁለት አባላትን በአዲስ ለመተካት የዕጩዎች ጥቆማ ማሰባሰብ የተጀመረው በሚያዝያ መጀመሪያ ላይ ነበር። 

ለ21 ቀናት የተካሄደው የዕጩዎች ጥቆማ ሲጠናቀቅ፤ “በሶስት ዙር የማጣራት ስራዎች እንደሚከናወን” ሂደቱን ለማካሄድ የተቋቋመው ኮሚቴ ከአንድ ወር በፊት በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የምርጫ ቦርድ አባላትን ለሚመለምለው ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ የሚሆኑ ስምንት አባላትን የሰየሙት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ነበር። 

“ነባሩ ቦርድ ከነግዙፍ ችግሮቹ ቢያንስ አንድ ምርጫ በማካሄድ ልምድ ያገኘ በመሆኑ ቀጣዩን ምርጫ እንዲያካሂድ እድል ሊሰጥ ይገባል”

– መኢአድ፣ ኢህአፓ፣ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባላትን በተመለከተ በመግለጫቸው ካሰፈሩት የተወሰደ

ኮሚቴው በአዋጅ በተቀመጠለት መስፈርት መሰረት የለያቸውን ዕጩዎቹን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ስድስት ዓመት የስራ ዘመን ያላቸው የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ለፓርላማ ከቀረቡ በኋላ ሹመታቸው እንደሚጸድቅ በአዋጅ ተደነግጓል። 

መጪውን ምርጫ በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ያወጡት አራቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ “ነባሩ ቦርድ ከነግዙፍ ችግሮቹ ቢያንስ አንድ ምርጫ በማካሄድ ልምድ ያገኘ በመሆኑ ቀጣዩን ምርጫ እንዲያካሂድ እድል ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል። አሁን በስራ ላይ ካለው የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ ውስጥ የስራ ዘመናቸውን ሊጠናቀቅ የተቃረበው፤ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ውብሸት አየለ፣ ብዙወርቅ ከተተ እና ዶ/ር አበራ ደገፋ ናቸው።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም በ2011 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ፤ ለስራ አመራር ቦርድ የተመረጡ አባላት “ለአንድ ተጨማሪ የስልጣን ዘመን ሊሾሙ እንደሚችሉ” ይደነግጋል። ብዙወርቅ እና ዶ/ር አበራ በድጋሚ በዕጩነት ቢቀርቡ፤ በምርጫ ቦርድ አባልነት የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ከአንድ ወር በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አራቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዛሬ መግለጫቸው፤ አዳዲስ የምርጫ ቦርድ አባላት የሚመረጡ ከሆነ  “ምርጫን የሚያህል ትልቅና ውስብስብ አገራዊ ኩነት ኃላፊነት በወሰዱ በጥቂት ወራት ውስጥ መርተው እውን ለማድረግ ልምድ የሚጎድላቸው” በመሆኑ “ስጋት ያጭራል” ሲሉ በመግለጫቸው አስፍረዋል። በዚህ መልክ የሚመጡ የምርጫ ቦርድ አመራሮች፤ በገዢው ፓርቲ “የበዛ እጅ አዙር ፍላጎት የመሾም እድላቸው ሰፊ” መሆኑን በመጥቀስም ተጨማሪ ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል።

በዚህም ምክንያት ነባሮቹን የምርጫ ቦርድ አባላት “ከመተካት ይልቅ”፤ “የማጠናከር ስራ ብቻ እንዲሰራ” ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ሊሆን የማይችልበት ምክንያት ካለ እና የቦርድ አባላትን እንደ አዲስ መሾም የግድ ከሆነ፤ በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ በተደነገገው መሰረት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ምክክር እንዲደረግ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሯ” ቤርሳቤህ ገብረ ለእዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጋለች]