በጋምቤላ ክልል ያሉ ስደተኞችን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ “የተሳሳቱ መረጃዎች” “በእጅጉ እንዳሳሰቡት” ተመድ ገለጸ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR)፤ በጋምቤላ ክልል የተጠለሉ ስደተኞች ላይ በማነጣጠር በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ “የተሳሳቱ መረጃዎች” “በእጅጉ እንዳሳሰቡት” ገለጸ። ለሁኔታው በአፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት በአካባቢው ውጥረትን ሊያባብስ እንደሚችል ድርጅቱ አስጠንቅቋል። 

የተመድ የስደተኞች መርጃ ተቋሙ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው፤ ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 14፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው። ድርጅቱ በዚሁ መግለጫው፤ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በሀገራቸው ከሚደርስባቸው ጥቃት “ደህንነትን እና ጥበቃን ለማግኘት” እንደሆነ አስታውሷል። 

የጥገኝነት ሲቪል እና ሰብአዊ ባህሪያት “ለድርድር የማይቀርብ መርህ” መሆኑን በመግለጫው አጽንኦት የሰጠው ድርጅቱ፤ “በትጥቅ እንቅስቃሴ” ውስጥ ሲሳተፍ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በሀገሩ ሕግ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን አመልክቷል። ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ መረጃዎች፤ ከደቡብ ሱዳን ተፈናቅለው በጋምቤላ ክልል ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች በክልሉ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ግጭት ውስጥ ተሳትፎ እንዳላቸው ወንጅለው ነበር።

UNHCR በዛሬው መግለጫው ስደተኞች ላይ ያነጣጠሩ “የተሳሰቱ መረጃዎች” መሰራጨታቸውን ቢገልጽም፤ ስለ መረጃዎቹ ምንነት በግልጽ ያለው ነገር የለም። በጋምቤላ ክልል ባሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ የቀረበውን ውንጀላ፤ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎችም ሆነ ከገለልተኛ አካላት ማጣራት አልቻለችም። 

እስካለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ድረስ በጋምቤላ ክልል ተጠልለው የሚገኙ ስደተኞች ብዛት 482,981 እንደሆነ ከተመድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ስደተኞቹ በክልሉ በሚገኙ ንጉኑየል፣ ቲርኪዲ፣ ኩሌ፣ ጀዊ እና አኩላ በተባሉ አምስት መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ።

የተመድ የስደተኞች መርጃ ተቋም በዛሬ መግለጫው፤ በጋምቤላ ከሰሞኑ በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ እና የውሃ አቅርቦትን ጨምሮ አንዳንድ አገልግሎቶቹ በጊዜያዊነት ለማቋረጥ መገደዱን አስታውቋል። ሁኔታዎች ሲፈቀዱ አገልግሎቱን እንደሚያስቀጥልም ጠቁሟል።

በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ሳምንት በተቀሰቀሰ “ግጭት” እና “የጸጥታ መደፍረስ” የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መደበኛ እንቅስቃሴ መቆሙን ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መግለጻቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ይህንኑ እውነታ አረጋግጧል።  

በክልሉ ከስደተኞች ጋራ በተያያዘ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን UNHCR በዛሬው መግለጫው ላይ አስታውቋል። የስደተኞቹን፣ የአስተናጋጆቻቸውን እና የሰብአዊ ሰራተኞች ደህንነትን ለማስጠበቅ ከባለሥልጣናት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል። በጋምቤላ ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ ያቀረበው ድርጅቱ፤ ስደተኞችን እና አስተናጋጅ ማህበረሰቦችን አደጋ ላይ ከሚጥል “የጥላቻ ንግግር” እንዲታቀቡ ለሁሉም ሰው መልዕክት አስተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)