ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሲተገበር የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) መርሃ-ግብር “ስህተት” እንደነበር የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ። በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት እንዲሆኑ፤ ዜጎች የተመዘገቡበት መንገድ “ትክክል አልነበረም” ሲሉም ተችተዋል።
ወ/ሮ ጫልቱ ይህንን ያሉት፤ የሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ያስገነባቸው ቤቶች ለምርቃት መብቃታቸውን በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 5፤ 2018 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። በቤተሰብ ደረጃ 150 ሰዎችን እንዲይዙ ተደርገው የተገነቡት እነዚህ ቤቶች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተመረቁት ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ነበር።
የቤቶቹ ግንባታ፤ ሚኒስቴሩ በተለያዩ ቦታዎች ሲያከናውናቸው የቆያቸው “የገጠር ከተሞችን የማልማት” እና “ሞዴል መንደርን የመመስረት” ሂደት አካል መሆኑን አስታውቋል። መስሪያ ቤቱ በስሩ ከሚገኙ የተጠሪ ተቋማት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያስገነባቸው እነዚህ መኖሪያ ቤቶች፤ በኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ሰበታ ሀዋስ ወረዳ፣ በቱሉ አራራ ከተማ የሚገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2013 ይፋ ባደረገው የልማት ዕቅድ፤ በገጠር በ10 ዓመት ውስጥ እንዲገነቡ የታቀዱ የመኖሪያ ቤቶች ብዛት 2.8 ሚሊዮን ነው። ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም. ባሉት በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ 4.4 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች በከተሞች እንዲገነቡ በዕቅዱ ተይዟል። ባለፉት አምስት የእቅዱ ዓመታት የተገነቡ ቤቶች አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሰኔ ወር ለፓርላማ አባላት ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ አመልክተው ነበር።
በወቅቱ 256 ሺህ ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የፓርላማ ማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል። አብይ በጳጉሜ 4፤ 2017 በተከናወነው የህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ መንግስታቸው በሚቀጥሉት አምስት እና ስድስት ዓመታት “1.5 ሚሊዮን ቤቶች” ለመገንባት ማቀዱን ተናግረዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤት ግንባታ ሜጋ ፕሮጀክት፤ መንግስታቸው በ10 ዓመት ውስጥ በከተማና በገጠር ለመገንባት በልማት እቅዱ ከያዘው 7.2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት በመንግስት፣ በግል እንዲሁም በመንግስትና በግል ትብብር የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች፤ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለመገንባት ከታቀዱት ጋር ሲዳመር የሚመጣው 2.5 ሚሊዮን ቤቶች ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም በእቅድ የያዛቸውን የቤት ልማት ፕሮጀክቶች “በአግባቡ መጨረስ አለመቻሉን” የታዘቡ ባለሙያዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ባደረጉት ዕቅድ ተግባራዊነት ላይም ጥርጣሬ አላቸው። በመንግሥት የታቀዱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በወቅቱ መጨረስ ያልተቻለው፤ በመርሃ-ግብሩ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል።
ባለፉት 17 ዓመታት በከተሞች ሲተገበር የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፤ በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር “በተወሰነ ደረጃ ያቃለለ” መሆኑን በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ የጠቀሱት ወ/ሮ ጫልቱ፤ ሆኖም መርሃ-ግብሩ “ስህተት” እንደነበር ገልጸዋል። መርሃ-ግብሩ “የመንግሥት ተሳትፎ የበዛበት” እና “ሁሉንም ዜጎች የቤት ባለቤት ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ” መሆኑ “ስህተት” እንደሆነም አስረድተዋል።
ሚኒስትሯ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሃ ግብር ጋር በተያያዘ የነቀፉት ሌላው ነጥብ፤ የቤት ፈላጊ ዜጎች ምዝገባ የተከናወነበት መንገድ ነው። የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲገነቡ መጀመሪያ የታለመው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቢሆንም፤ አብዛኞቹ በቤቶች ውስጥ የሚኖሩት ግን “ተከራዮች” መሆናቸው በሚኒስትሯ መግለጫ ላይ ተነስቷል።

“በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ብናይ ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የተመዘገበበት [አካሄድ] ትክክል አልነበረም። ቤቶቹ ከተገነቡ በኋላም የሚኖሩባቸው ሰዎች በአብዛኛው ተከራዮች ናቸው። ፕሮግራሙም ላለው የሚጨምር እንጂ ቤት የሌላቸው ዜጎችን ለይቶ ችግራቸውን የሚፈታ አልነበረም” ሲሉ ወ/ሮ ጫልቱ ተችተዋል።
የከተማና ልማት ሚኒስቴር በ2012 ዓ.ም አሻሽሎ ባወጣው የቤት ልማት ስትራቴጂ ከተጠቀሱ ስምንት የከተማ ቤት አቅርቦት አማራጮች መካከል ቢያንስ ሁለቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ። መንግስት ተግባራዊ ሲያደርገው በቆየው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሃ ግብር ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩት እነዚህ አማራጮች 10/90 እና 20/80 የቁጠባ እና የመንግስት ድጋፍ አሰራሮች ናቸው።
በተመሳሳይ መልኩ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመው አሰራር 40/60 ቁጠባ እና የመንግስት ድጋፍን የያዘ ነበር። በቀደሙት ዓመታት ሲተገበር የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሃ-ግብር “ሁሉንም ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግ ያሰበ” እንደነበር የከተማና ልማት ሚኒስትሯ በዛሬው መግለጫቸው አስታውሰዋል።

“መንግስት ሁሉም ዜጋ ቤት ቢኖረው ደስተኛ ነው” ያሉት ወ/ሮ ጫልቱ፤ “ይህ ግን የሚሳካ አይደለም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሚኒስትሯ በመንግስት ወጪ ብቻ በሚገነቡ ቤቶች፤ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ እንደማይቻልም አጽንዖት ሰጥተዋል።
በአዲሱ የቤቶች ልማት ፖሊሲ፤ መንግስት በቤቶች ግንባታ ዙሪያ ያለው ተሳትፎ “20 በመቶ ብቻ” እንደሚሆን ሚኒስትሯ አስረድተዋል። ፖሊሲው የሌሎች ሀገራትን ፖሊሲ ልምድ በመውሰድ እንደተዘጋጀ የገለጹት ወ/ሮ ጫልቱ፤ ቀሪው 80 በመቶ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በባለሀብቶች፣ በቤት አልሚ ኩባያንዎች እና በተለያዩ አማራጮች እንዲመለስ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የነበራት “የከተማ ልማት ፖሊሲ” ብቻ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሯ፤ “የቤት ልማት ፖሊሲ” በሀገር ደረጃ አለመዘጋጀቱ ለዜጎች አንገብጋቢ የሆነው የመኖሪያ ቤቶች ጉዳይ “ትኩረት እንዳይሰጠው” እንዳደረገው አመልክተዋል። አዲሱ የቤት ልማት ፖሊሲ የተዘጋጀው፤ “በከተማ እና በገጠር ልማት ለሚኖሩ ሁሉም ዜጎች፣ አቅምን ያገናዘበ፣ ተደራሽ እና በቂ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ታህሳስ 28፤ 2018 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው፤ ለውይይት ካቀረባቸው አጀንዳዎች ውስጥ ይኸው ፖሊሲ አንዱ ነበር። የቤት ልማት ፖሊሲው በውይይቱ የተነሱ ግብአቶች ከታከሉበት በኋላ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “በሙሉ ድምጽ” ማጽደቁንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በባለፈው ሳምንት መግለጫው አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























