ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የቆዩት አብይ አህመድ፤ በስልጣናቸው ላይ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት እንዲቆዩ በፓርላማ ይሁንታ አገኙ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ ሰኞ መስከረም 25፤ 2019 በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ሹመታቸው በጭብጨባ ጸድቆላቸዋል።
በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት የፌደራል መንግስትን ስልጣን የሚረከበው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ነው። ከሶስት ወራት በፊት በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 438 አብላጫ የፓርላማ መቀመጫዎችን በማግኘት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የተቆጣጠረው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው።
በፌደራል መንግስት “ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ስልጣን” ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመረጠው፤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል እንደሆነ በስራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ይደነግጋል። በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በድጋሚ በዕጩነት ያቀረበው፤ በጅማ ዞን ጎማ 2 የምርጫ ክልል ለፓርላማ የተመረጡትን አብይ አህመድን ነው።

አብይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት፤ ለአምስት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ይዘው የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን በመተካት ነው። በመሪነት መንበር ላይ ለሶስት ዓመት ከመንፈቅ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ከስድስተኛው ዙር ምርጫ በኋላ በመስከረም 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የመንግስት ምስረታ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው የሰባተኛው የምርጫ ዘመን የመንግስት ምስረታም፤ አብይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸው እንዲቀጥሉ በአዲሱ ፓርላማ ይሁንታ አግኝተዋል። ይህንን ተከትሎም አብይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት ቆመው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በቃለ መሃላ ስነ ስርዓቱ ይፋ የተደረገው የአዲሱ መንግስት ምስረታ፤ ከአምስት በፊት በመስቀል አደባባይ ከተከናወነው በዓለ ሲመት ከፍተኛ ልዩነት የታየበት ነው። መስከረም 24፤ 2014 የተካሄደው ይህን ስነ ስርዓት፤ ሰባት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች እና ህዝብ ታድመውታል።

በሰባተኛው የምርጫ ዘመን የመንግስት ምስረታ ይህን መሰል ስነ ስርዓት እንደማይኖር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በይፋ የገለጹት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ነበር። በዚሁ ጊዜ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታ፤ ከአምስት ዓመት በፊት እንደነበረው “ጊዜ ማባከን አስፈላጊ ነው ብዬ እኔ አላምንም” ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፓርላማ ጠዋት የሚመርጠውን ከመረጠ በኋላ ወዲያው ወደ ስራ መግባት እንጂ እንግዳ ስንቀበል፣ እንግዳ ስንሸኝ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ አይደለም” ሲሉም በወቅቱ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































