የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ 

ላለፉት ስምንት ዓመታት የገንዘብ ሚኒስቴር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ አህመድ ሽዴ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛው አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ። አቶ አህመድን በአፈ ጉባኤነት የመረጡት፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 25፤ 2019 የሰባተኛ የምርጫ ዘመን የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ያካሄዱት አዲስ ተመራጭ የፓርላማ አባላት ናቸው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የተሰጠባቸው 501 መቀመጫዎች ናቸው። ምርጫ ከተካሄደባቸው ከእነዚህ መቀመጫዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውጤታቸው የጸደቀው የ486ቱ ነው።

ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት መሰረት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ 438 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቆጣጠር፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች 40 መቀመጫዎች አግኝተዋል። የግል ዕጩዎች በበኩላቸው ስምንት መቀመጫዎች አግኝተዋል።

በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመክፈቻ ስብሰባ የተገኙት ተመራጮች፤ ፓርላማውን በአፈ ጉባኤነት እንዲመሩ በዕጩነት የቀረቡትን አቶ አህመድ ሽዴን በሙሉ ድምጽ መርጠዋል። አቶ አህመድ ከዚህኛው ሹመታቸው በፊት በሚኒስትርነት ባገለገሉበት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፤ ለስምንት ዓመታት በሚኒስትር ዴኤታነት አገልግለዋል።

አቶ አህመድ በገንዘብ ሚኒስትርነታቸው ከመሾማቸው አስቀድሞ የትራንስፖርት እና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነውም ሰርተዋል። አቶ አህመድ ወደ ፌደራል ከመምጣታቸው በፊት፤ በሶማሌ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎችን ለ10 ዓመታት በኃላፊነት መርተዋል።  

ከሚኒስትርነት ወደ አፈ ጉባኤነት የተዛወሩት አቶ አህመድ፤ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ከአፈ ጉባኤነታቸው የተሰናበቱት አቶ ታገሰ ጫፎን የሚተኩ ይሆናሉ። አምስተኛው የፓርላማው አፈ ጉባኤ የሆኑት አቶ ታገሰ፤ ለስምንት ዓመታት በዚሁ የኃላፊነት ቦታ ላይ ቆይተዋል።

ከእርሳቸው በፊት ለሰባት ወራት ብቻ በአፈ ጉባኤነት ያገለገሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው። ወ/ሮ ሙፈሪያት በአፈጉባኤነት የተመረጡት፤ እንደ አቶ ታገሰ ሁሉ ለስምንት ዓመታት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው። 

ከአቶ አባዱላ በፊት ለአምስት ዓመታት የፓርላማ አፈ ጉባኤ የነበሩት አቶ ተሾመ ቶጋ ናቸው። ለአቶ ተሾመ አፈጉባኤነቱን ያስረከቡት አቶ ዳዊት ዮሐንስ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከምስረታው አንስቶ ለ10 ዓመት ያህል በአፈ ጉባኤነት በመምራት ቀዳሚ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)