ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ግጭቶች በገጠማቸው ሀገራት፤ ኤል ኒኞ “ከባድ ጫና” እንደሚያስከትል የተመድ ተቋማት አስጠነቀቁ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች “ተጨማሪ ግጭት ሊቀሰቅሱ” እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ ጉዳዮች እና የድንገተኛ እርዳታ አስተባባሪ ቶም ፍሌቸር አስጠነቀቁ። ቀጠናው ለተጋረጡበት የኤል ኒኞ ክስተቶች፣ ነባር ሰብአዊ ቀውሶች፤ ግጭቶች እና መፈናቀሎች “በተናጠል” መፍትሔ ማበጀት እንደማይቻልም አስተባባሪው አሳስበዋል።

ከግጭት አዙሪት መውጣት በተሳናቸው የቀጠናው ሀገራት እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ “የከፋ ሊሆን ይችላል” ተብሎ የሚጠበቀው የኤል ኒኞ የአየር ጠባይ ሁኔታ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) እና የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አስጠንቅቀዋል። የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ የተደመጠው፤ ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 11፤ 2019 በስዊትዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ  በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በመጪዎቹ ወራት የኤል ኒኞ የአየር ጠባይ ዋና ማዕከል በሆነው እና ከምድር ገጽ አንድ ሶስተኛውን በሚሸፍነው የፓሲፊክ ውቅያኖስ የሙቀት መጠን፤ ከአማካኝ በላይ እስከ 3.8 ዲግሪ ሴሊሺየስ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ሴሌስቴ ሳውሎ ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት በህዳር እና ታህሳስ ወራት ይበረታል ተብሎ የሚጠበቀው ኤል ኒኞ፤ በዓለም የአየር ጠባዮች ላይ “ከባድ መዘዝ” እንደሚያስከትል ዋና ጸሀፊው ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ፎቶ፦ UNDP Ethiopia

ኤል ኒኞ የሚያስከትለው የአየር ጠባይ ለውጥ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ከባድ ድርቅ፤ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ኃይለኛ ዝናብ እና ጎርፍ ያስከትላል። ኢትዮጵያ በምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ከተለመደው በላይ እርጥብ የአየር ሁኔታ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ ስጋትን እንደሚጨምር ሴሌስቴ ሳውሎ ገልጸዋል።

በሰሜን እና በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ወራት፤ የኤል ኒኞ ክስተት በተለምዶ ከደረቅ የአየር ጠባይ ጋር ይያያዛል። በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ እና ምስራቅ ሀረርጌ አካባቢዎች እንዲሁም ግጭቶች ባሉባቸው የሰሜን አማራ እና የትግራይ አካባቢዎች፤ ያለፈው ክረምት እስከ አራት ሳምንታት በመዘግየቱ በአካባቢዎቹ ድርቅ ተከስቷል።

በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን (IFRC) የተቋቋመው የአደጋ ጊዜ ፈጣን እርዳታ ፈንድ ባለፈው ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በትግራይ እና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ ወረዳዎች በአጠቃላይ 250,035 ሔክታር የእርሻ ሰብል ወድሟል።  በሪፖርቱ መሰረት በምዕራብ ሀረርጌ፣ በሰሜን ጎንደር እና በትግራይ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች የ28,629 የቤት እንስሳት ሞት ተመዝግቧል።

IFRC ባለፈው ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በትግራይ እና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ ወረዳዎች በአጠቃላይ 250,035 ሔክታር የእርሻ ሰብል ወድሟል። 

ኢል ኒኞ ያስከተለው ድርቅ በተጫናቸው በእነዚህ አካባቢዎች ከ319 በላይ የውሃ ምንጮች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመድረቃቸው፤ በነዋሪዎች እና የቤት እንስሳት ላይ “ከፍተኛ ስጋት” እንደተጋረጠ ሪፖርቱ ጠቁሞ ነበር። የአፋር ክልልን ጨምሮ በአብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ድርቅ ያስከተለው የኤል ኒኞ ክስተት፤ በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል በአንጻሩ የተጠናከረ ዝናብ የመፍጠር “90 በመቶ ዕድል” እንዳለው የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። 

ኤል ኒኞ በሚያስከትለው ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅ እና ጎርፍ ምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ እስያ እና የፓሲፊክ ቀጠና ጉዳት እንደሚደርስባቸው የተናገሩት ቶም ፍሌቸር፤ ክስተቱ “ከባድ ሰብአዊ መዘዝ” እንደሚያስከትል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ክስተቱ በሚያመጣቸው የአየር ጠባይ ለውጦች፤ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ረሃብ እንደሚያጋጥማቸው የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ተናግረዋል። 

የኤል ኒኞ ቀውስ በዓለም ዙሪያ በተንሰራፉ ግጭቶች ላይ የሚታከል እንደሆነ ያስታወሱት ቶም ፍሌቸር፣ የነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ምግብ ዋጋዎች መናር ችግሩን እንደሚያወሳስቡ ተናግረዋል። በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) መረጃ መሰረት፤ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በግጭት እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ምክንያት ወደ 16 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የምግብ ዋስትና እጦት አለባቸው። 

ካርታ፦ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP)

የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ የኤል ኒኞ ቀውስ በክስተቱ በተጎዱ ሀገራት ብቻ ተገትቶ የሚቆይ አይደለም ባይ ናቸው። ይልቁንም ክስተቱ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ቀውስ ሊያስከትል፣ ግጭቶችን እና መፈናቀልን ሊያባብስ ይችላል የሚልስ ስጋት አላቸው። 

ይህ ክስተት በተለይ የአፍሪካ ሀገራትን ከ10 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ሊያስወጣቸው እንደሚችል እና አጠቃላይ የሀገራዊ የምርት መጠናቸው ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል የአፍሪካ ልማት ባንክን ስሌት ዋቢ አድርገው ቶም ፍሌቸር ተንብየዋል። ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እርምጃዎች ለመውሰድ፤ በተለይ መጪዎቹ ሁለት ሳምንታት “ቁልፍ” ጊዜ እንደሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለኤል ኒኞ ክስተት ተጋላጭ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ፤ ከባድ ዝናብ መጣል ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ሊቀርብላቸው እንደሚገባ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ አሳስበዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 ሀገራት በኤል ኒኞ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመደገፍ፤ የመንግስታቱ ድርጅት 50 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ በትላንትናው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ተደርጓል። 

ፎቶ፦ ኤሌማ ኦኪች/ ተመድ

ገንዘቡ ከተመደበላቸው ሀገራት መካከል የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑት ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል።  እነዚህ ሀገራት በሚገኙበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚደረጉ ግጭቶች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የገለጹት የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ፤ “ዘላቂ፣ ቆራጥ እና መፍትሔ ማበጀት” የሚችል ዲፕሎማሲ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

We are hiring!